ለንብና ዶሮ እርባታ ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከNORAD ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በሲዳማ ክልል በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ለማሳደግ ያለመ ተግባር ተኮር የአቅም ግንባታ ስልጠና በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች በንብ ማነብና ዶሮ እርባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎች መስጠት ጀምሯል።

የም/ቴ/ሽ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ የስልጠናውን መጀመር ባስታወቁበት ንግግራቸው ግብርና ከዓመታዊ ሀገራዊ ምርታችን ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስድ እንደመሆኑ ይህንን ዘርፍ እስካላዘመንንና ምርታማነቱን እስካላሳደግን ድረስ የሚፈልገውን ሁለንተናዊ ብልጽግናና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል። ዶ/ር ታፈሰ አክለውም በሲዳማ ክልል በእንስሳት እርባታ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ ለመስራት የሚያስችሉ የመልከአምድር አመቺነት፣ በቂ የሰው ኃይልን ጨምሮ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ስለሚገኝ ይህንን እድል ለመጠቀም ባለሙያውን የማብቃት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተሩ አቶ ማርቆስ ፍሰሀ በበኩላቸው ስልጠናው ከኖራድ ፕሮጀክት ድጋፍ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው ቁጥራቸው ከ100 በላይ ለሚሆኑ ባለሙያዎች በንብ ማነብና ዶሮ እርባታ ዙሪያ ያለባቸውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ተግባር ተኮር የሆነ ሳይንሳዊ ስልጠና በዩኒቨርሲቲው የዘርፉ ምሁራን እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል እንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆንባ በስልጠናው ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት በንብ ማነብና ማር ምርት፣ ዶሮ እርባታ እንዲሁም የወተትና ወተት ተዋጽኦ ምርት ላይ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ሰፊ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ባለበት በዚህ ወቅት ከዩኒቨርሲቲው እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በሲዳማ ክልል ደረጃ 60 የሚደርሱ የማር አምራች መንደሮችና በርካታ የዶሮ አርቢ ማህበራት እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው ስልጠናውን የሚወስዱ ባለሙያዎች ወደየመጡበት አካባቢ ሲመለሱ ይህንን እውቀት ለአርብቶአደሮችና ለማህበራት በማስተላለፍ ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድጉ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et