የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅን ጎበኙ::
በተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ የተመራው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅን የጎበኙ ሲሆን የኮሌጁ ቺፍ ኤግዘኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዓለሙ ጣሚሶ የኮሌጁን አጠቃላይ አሁናዊ ቁመና: የስራ እንቅስቃሴ: ጠንካራና ዳካማ ጎኖች ተብለው የተለዩ እንዲሁም ልዩ ትኩረት በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት በኮሌጁ ስር የሚተዳደሩ የተለያዩ የጤና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ቢኖሩም አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ልዩ ልዩ የህክምና ክፍሎችና የኮሌጁ የተማሪዎች አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በትኩረት ምልከታ ተደረጎባቸዋል።
ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ከጉብኝት መልስ በተካሄደው ውይይት ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው ኮሌጁ በስሩ የሚገኙ ባለምጡቅ አእምሮ ባለሙያዎቹን በማስተባበር ከአከባቢው ባሻገር በጎረቤት ሀገሮች ያሉ ዕድሎችን ለመጠቀምና ሐዋሳ ከተማን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በትጋት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል። ዶ/ር ችሮታው ከትምህርት ጥራት ጎን ለጎን የተማሪዎችን የምግብና የመኝታ አገልግሎቶች ደረጃውን የጠበቀ በማድረግ ተመራጭነታችንን ማሳደግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጉድኝቶችና ትብብሮችን ማጠናከር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ተ/ፕሬዝዳንቱ በውስጥ አቅም ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን ግዜ ሳይሰጡ መፍታትና ከዚያ በላይ የሆኑትን ደግሞ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ብሎም መንግስት እንዲያግዟቸው ማሳወቅ እንዳለባቸው ለኮሌጁ አስተዳደር የሥራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይም በዩኒቨርሲቲ ስር የሚተዳደሩ ሆስፒታሎችን የሥራ ማስኬጃ በጀት በተመለከተ በልዩ ትኩረት ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር ተነጋግሮ መፍትሄ እንዲሰጠው የሚችሉትን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል::
በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የአስተዳደርና ልማት: የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የአካደሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንቶች የየበኩላቸውን ምላሽ ሰጥተዋል።