በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተፈረመውን ቁልፍ የአፈጻጸም ማሳያዎች የያዘ ሰነድ ተግባራዊ ለማድረግ በፕሬዚደንቱ እና በምክትል ፕሬዚደንቶች እንዲሁም የፕሬዚደንት ጽ/ቤት ኃላፊ መካከል የፊርማ ስነ-ስርዓት ታህሳስ 23/2017 ዓም ተካሂዷል::
በፊርማ ስነ ሥርዓቱ መግቢያ ላይ የፕላንና ስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ቡርቃ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትና የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተፈራረሙት ቁልፍ የአፈፃፀም አመላካቾች ዝርዝር ይዘት ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ይህንኑ ሰንድ በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎች በየዘርፋቸው የሚወስዱትን የቤት ሥራ ወደ ፈፃሚዎች ለማውረድ ውል እንደሚገቡ ገልፀዋል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ከሳምንታት በፊት በዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንቶችና በትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች መካከል የተፈረመው ሰነድ ቀደም ሲል ለዩኒቨርሲቲዎች በኮታ ሲሰጥ የነበረውን የበጀት ድልድል በማስቀረት በአፈጻጸማቸው መሰረት የሚደለድል በመሆኑ ተወዳዳሪና ጠንካራ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ መገኘት የምርጫ ብቻ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሬዚደንቱ አክለውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር የአፈጻጸም ውል ስምምነት (performance contracting agreement) ዋነኛ አላማ ተቋማቱ የአስተዳደር ቅልጥፍናና ውጤታማነትን በማሻሻል፣ የትምህርት አሰጣጥ ጥራትን በማሳደግ፣ የምርምር ስራዎች ጥራትና ተጽዕኖ በመጨመር እንዲሁም ጠንካራ የማህበረሰብ ተሳትፎን በማረጋገጥ ለሀገር ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።
"ስትራቴጂክ ሰነዶች ተቀርፀው ብቻ እንዲቀሩ ሳይሆን ወደ ፈጻሚ አካላት በማውረድ ተፈጻሚነታቸውን መከታተልና ማረጋገጥ ይገባል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀሪው ግማሽ ዓመት ውስጥ ለሚኖረው ሥራ በተመሳሳይ የውል ስምምነት በም/ፕሬዚደንቶችና ዲኖች እንዲሁም በፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊና በዳይሬክተሮች/ሥራ አስፈፃሚዎች መካከል እንደሚፈረም ገልፀው ለተፈጻሚነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የላቀ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በፊርማው ስነ ሥርዓት ላይ የሁሉም ኮሌጅ ዲኖችና ተባባሪ ዲኖች: የኢንስቲትዩት ዳይሬክተሮችና ምክትሎቻቸው እንዲሁም ሁሉም የዘርፍ ዳይሬክተሮችና ሥራ አስፈፃሚዎች የተገኙ ሲሆን አሰራሩ ቁጥጥርን በማሳደግ የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ አፈጻጸም እንደሚያሳድግ እምነት ተጥሎበታል።