በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ስር የሚገኘው የማኑፋክቸሪንግ ምህንድስና ፋካልቲ በራሱ መምህራን ያሰራቸውን ለሀይድሮሊክስ ቤተሙከራ የሚያገለግሉ ማሽኖች ከ24 በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሠርቶ አስረክቧል።
የፋካሊቲው ዲን ዶ/ር ካሳሁን ጋሹ እንዳሉት የማኑፋክቸሪንግ ፋካሊቲ በስሩ ስድስት የትምህርት ክፍሎች ሲኖሩት በስራቸው ባሉ ወርክሾፕ ላቦራቶሪዎች ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በተለይ ከ2014 ዓ.ም በኋላ የዩኒቨርስቲያችንን የትኩረት አቅጣጫ ልየታ ተከትሎ ፋካሊቲው የተለያዩ ገቢ የሚያመነጩ ሥራዎችን መሥራት መጀመሩን የጠቆሙት ዶ/ር ካሳሁን የማሽን ሾፕ ውስጥ ከሰባት ዓመታት በላይ ካለ ሥራ የተቀመጡ ከ15 በላይ ቀላልና ከባድ ማሽኖችን የፌደራል ኦዲተር በ2014 ከላከልን በኃላ በራሣችን መምህራን በመጠገን ወደ ምርት አስገብተናቸዋል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ይገቡ የነበሩ ለሀይድሮሊክስ ላቦራቶሪ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ማሽኖች በፋካሊቲው መምህራን በተሻለ ጥራት ተሰርተው እና የአእምሯዊ ንብረት ባለቤትነት እውቅና ተሰጥቷቸው እስካሁን ለ24 የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ማስረከብ እንደቻሉ ዲኑ ገልፀዋል::
በቀጣይም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ባደረግናቸው የመሥክ ዳሰሳ ጥናት ፍላጎቶችን ስላየን ወደሥራ ለመግባት የመግባቢያ ሠነዶችን ለመፈራረም በሒደት ላይ እንገኛለንም ብለዋል።
ዶ/ር ካሳሁን በሀዋሳ ዩኒቨርስቲና በሀዋሳ እንዳስትሪ ፓርክ በጋራ እየተሠራ ያለውን "Experimental Investigation and Implementation Automantion and Sludge Mangement System" በሚል ርዕስ የተሰጠው የቴማቲክ ፕሮጀክት ተንተርሶ ሙሉ በሙሉ ወርክሾፓችን pilot prototype አምርቶ በመጨረስ ለሙከራ አዘጋጅቷል ብለዋል።
የእነዚህ ማሽኖች የፈጠራ ባለቤትነት እውቅና ያላቸው ሁለት መሀንዲሶችን በዎርክሾፕ ውስጥ ተገኝተን ያነጋገርናቸው ሲሆን የማሽን ማምረት ስራውን እስከ 16 ሰዎች እንደሚሳተፉበትና በዋጋም ሆነ በጥራት ከውጭ አገር ከሚገዙት ማሽኖች እጅግ የተሻሉትን ማምረት እንደቻሉ አስረድተውናል::
ኢንጂነር ፍሬው ስለሺ ማሽኖቹ ከእንግሊዝና ከጀርመን የሚገቡትን የሚተኩ እንደሆነ ጠቅሶ በውሃ ምህንድስና ቤተ ሙከራዎች ውስጥ ሲሙሌተር: የውሃ ስነ ባህሪ መመርመርያ: የግድብ አሰራር መቆጣጠርያና የመሳሰሉትን ተግባር ተኮር ትምህርት ለመስጠት እጅግ አስፈላጊ ግብዓት መሆናቸውን አስረድቶናል:: ከስድስት ዓመታት በፊት የጀመሩት የፈጠራ ስራ አሁን ላይ ሰባት ማሽኖች ላይ መድረሱን የጠቀሰው መ/ር ፍሬው ድጋፍ ከተደረገላቸው ብዙ መስራት እንደሚችሉ ገልጽዋል::
ኢንጂነር መኮንን በቀለ በበኩሉ እስካሁን ከሰሩት ሰባት ማሽኖች በተጨማሪ ሙሉ የሃይድሮሊክስ ላብራቶሪን ማቋቋም ደረጃ መድረሳቸውን ጠቅሶ ከውጪ የሚመጣውን ማሽን ዋጋ በብዙ እጥፍ ባነሰ ዋጋ ለዩኒቨርሲቲዎች አስረክበው መተው ሳይሆን ከ100 ገፅ በላይ ያለው ማኑዋል አዘጋጅተው አብረው እንደሚያስረክቡና ለላብራቶሪ ባለሙያዎችም ስልጠና እንደሚሰጡ ተናግሯል::
የማኑፋክቸሪንግ ምህንስና ፋካልቲ ማሽን ዎርክሾፕን ሥራ የጎበኙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ባዩት ነገር እጅግ መደሰታቸውን ገልፀው ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር ለመስራት የሚፈልጉ ማንኛውም ተቋማት አብሮ ለመስራትና መሃንዲሶቹንም በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳውቀዋል::