የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሀገሪቱን እድገትና የህዝቡን ህይወት ለማሻሻል ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስገነዘቡ።
ትምህርት ሚኒስቴር ከአርባ ሰባት (47) የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በ2017 የሚተገበር ቁልፍ የአፈጻጸም ውል ተፈራርሟል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በስምምነቱ ወቅተት እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሯቸው ምርምሮችና የሚያፈሯቸው ዜጎች አገር የሚለውጡና ከዓለም ጋር ተወዳድረው ማሸነፍ የሚችሉ ሊሆኑ ይገባል።
ዩኒቨርስቲዎች ራሳቸውን ወደ ራስገዝነት እያሳደጉ እድገታቸውንና ቀጣይነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸውም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተፈረመው ውል ሃላፊነትና ተጠያቂነትን በማስፈን የትምህርት፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ጥራት ለማስጠበቅ እንደሚያስችልም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያ ስምምነቱ መሠረት ውጤት የሚያስመዘግቡ ተቋማት በበጀት ጭምር የበለጠ የሚደገፉበት፣ ወደ ኋላ የሚቀሩና ዝቅተኛ አፈጻጸም የሚያስመዘግቡት ደግሞ ተጠያቂ የሚሆኑበት እንደሆነም ጠቁመዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው የቁልፍ ስራዎች አፈጻጸም ውሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይንሳዊና ዓለም አቀፋዊ መለኪያዎች ላይ ያተኮረ እድገት እንዲኖራቸው እንደሚያስችል ገልጸዋል። ስምምነቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የክትትልና ግምገማ ስርዓት እንዲኖርና ዩኒቨርስቲዎች በተልዕኳቸው ላይ አትኩረው እንዲሰሩ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርተ ተቋማቱ በገቡት ስምምነት መሠረት ስራዎቻቸውን በየደረጃው በማውረድና ጠንክሮ በመስራት ቀጣይነት ያለው ውጤት ለማስመዝገብ መረባረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትሩን በመወከል የከፍተኛ ትምህርቶ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ ዩኒቨርስቲዎቹን በመወከል ደግሞ የየዩኒቨርስቲዎቹ ቦርድ ሰብሳቢዎችና ፕሬዚዳንቶች ፈርመዋል።