ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኤስ.ኦ.ኤስ ህጻናት መንደር ጋር ባለው የትብብር ፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ግምገማ አካሄደ፡፡
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኤስ.ኦ.ኤስ ህጻናት መንደር ሀዋሳ ፕሮግራም ጋር እየሰራበት ያለውን "ለአደጋ የተጋለጡ ህፃናት ፍላጎቶች ዘላቂ ምላሽ" ወይም "Sustainable response to the needs of children at risk" የተባለ የትብብር ፕሮጀክት አፈጻጸም ገምግሞ በቀጣይ ዕቅዶች ላይ ውይይት አካሂዷል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ መድረኩን ሲከፍቱ ፕሮጀክቱ በተለያየ ችግሮች ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ እንዲሁም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማገዝ ኑሯቸውንና የነገ ተስፋቸውን የሚያለመልሙበትን መንገድ በመቀየስ ሰብአዊ ስራዎችን በመስራቱ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሲዳማና አጎራባች ክልሎች ላይ እያከናወነ በሚገኝባቸው የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቡንና በቀጣይም ኤስ.ኦ.ኤስ.ን ከመሰሉ አጋር ድርጅቶች ጋር በቅርበት በመስራት የህብረተሰቡን ችግሮች በጋራ ለመፍታት የሚያስችሉ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን መንደፉን ተናግረዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲውና ኤስ.ኦ.ኤስ የህጻናት መንደር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በጋራ በርካታ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ሲወጡ መቆየታቸውን ጠቅሰው በተለይም ባለፉት ሶስት አመታት ሲተገበር የነበረው ይህ ፕሮጀክት ለአደጋ ተጋላጭ ልጆችን ለይቶ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ረገድ አዎንታዊ ውጤት ማስገንዘቡን ገልፀዋል።
የኤስ.ኦ.ኤስ ህጻናት መንደር ሀዋሳ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ጸጋዬ ደጀኔ በውይይት መድረኩ ፕሮጀክቱ በሶስት አመት ቆይታው ያከናወናቸው ሥራዎች ጠንካራና ደካማ ጎኖች የተለዩበት መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ሶስት አመታት በሚተገበረው አዲስ ፕሮጀክት ይዘት ላይ ማብራሪያ የተሰጠበት በመሆኑን እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል:: ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ለሁሉም ፕሮጀክቶች መሳካት ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለተወጣው ኃላፊነት ስራ አስኪያጁ አመስግነዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ከሲዳማ ክልል የተወጣጡ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የቱላ ክ/ከተማ እንዲሁም የኮቲ-ጀቤሳ ቀበሌ ተወካዮች ተገኝተው ገንቢ ሃሳብና አስተያየተቸውን ሰጥተዋል::