በአለምአቀፍ ደረጃ ለ33ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የ16ቱ ፀረ-ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ቀናት ማጠቃለያ መርሃግብር (የነጭ ሪቫን ቀን) "የሴቷ ጥቃት የኔም ነው! ዝም አልልም!" በሚል መሪ ቃል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ታህሳስ 4/2017 ዓም ተከብሯል።
ፕሮግራሙን ያስጀመሩት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ጾታዊ ጥቃት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚነካና የሚመለከት መልከ ብዙ ችግር በመሆኑ መፍትሔ ከማበጀት አንጻር ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በትብብርና በመግባባት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል። ዶ/ር ችሮታው አክለውም ጥቃቶችን መከላከል የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ በመጀመሪያ በጉዳዩ ዙሪያ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሚገባ በመሆኑ መሰል የግንዛቤ መፍጠርያ መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ምህረት ገነነ ቀኑ በአለምአቀፍ ደረጃ የሚከበረው የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን ለይተን ትግል እንዲደረግባቸው ከመንቀሳቀስ ባሻገር ቀኑን ማክበር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ድረስ የትኞቹን ጾታዊ ጥቃቶች ተጋፍጦ ማሸነፍ እንደተቻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። ጾታዊ ጥቃትን ለማስቀረት በቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር መከላከልና ማስቀረት ቢሆንም የዘመኑ ጥቃት መልኩን እየቀየረና እየተወሳሰበ መሄዱን ተከትሎ በየወቅቱ መሻሻል ቢኖርም ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት አለመቻሉን ወ/ሮ ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ፕ/ር ዘለቀ አርፍጮ ባስተላለፉት መልዕክት በሴቶች ላይ ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን የተዛባ አመለካከትና ምስል ለመቀየር መንግስት ባለፉት ጥቂት አመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ሴት አመራሮችን በመመደብ አዎንታዊ ስራ መስራቱን ጠቁመው ይህ እስከታች ድረስ ወርዶ አጠቃላይ የማህበረሰቡን አመለካከት በትክክለኛው መንገድ እስኪቀርጽ ድረስ ሊሰራ እንደሚገባው ተናግረዋል።
የበዓሉ ዋና ዓላማ ጾታዊ ጥቃቶችን በመከላከል ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማስቻል መሆኑን አስመልክቶ በዩኒቨርሲቲው መራሒት ክበብ አባላት የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራሞች ያቀረቡ ሲሆን የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።