የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የስትራቴጂክ ጉዳይ ስራ አስፈጻሚዎች ፎረም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀውና ከሁሉም የኢትዮጵያ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የስትራቴጂከ ጉዳይ ስራ አስፈጻሚዎችን የሚያሳትፈው የጋራ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ መድረኩን ባስጀመሩበት ንግግራቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስትራቴጂካዊ አመራር ከመስጠትና በዕቅድ ከመመራት አኳያ ክፍተቶች የሚታይባቸው መሆኑን አንስተው ለዚህ ክፍተት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ ብለዋል። በትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ ሰጪነት እየተተገበረ የሚገኘው የትኩረት ልየታና የራስ-ገዝነት አካሄድ ዩኒቨርሲቲዎችን ለሚቀርጹት ስትራቴጂ ተገዢ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ የጠቆሙት ዶ/ር ችሮታው የጋራ መድረኩ በተቋማቱ መካከል ልምድ በመለዋወጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የተቋማዊ ለውጥ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ከበደ ግዛው የውይይት መድረኩን ዓላማ አስመልክቶ እንደተናገሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስትራቴጂካዊ ስራ አስፈጻሚዎች የእስካሁኑን የስራ አፈጻጸም በመገምገም፤ በሴክተሩ ላይ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ አጀንዳዎችና የተለዩ የትኩረት አቅጣጫዎች ምን እንደሆኑ በመወያየት ቀጣይ ተግባራቸውን እንዲወስኑ ይረዳል ብለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የእቅድና በጀት ቡድን መሪ አቶ እሸቱ ገላዬ በበኩላቸው የውይይቱ አላማ ቀደም ሲል የነበረው የዩኒቨርሲቲ ፕላን ዳይሬክቶሬት ወደ ስትራቴጂክ ጉዳዮች በመቀየሩ በአዳዲስ የስራ አስፈጻሚዎች መካከል የእርስ በርስ የትውውቅ መድረክ በመሆን እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለማጠንከር መሆኑን ተናግረዋል። በተለያዩ ምክንያቶች መሰል የውይይት መድረክ ሳይከናወን ከሁለት አመት በላይ መቆጠሩን የገለጹት አቶ እሸቱ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውይይቱ እንዲሳካ ላደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል::