ደረጃ ዶት ኮም እና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ቀጣሪ ድርጅቶችን ከአዳዲስ ስራ ፈላጊ ተመራቂዎች ጋር ለማገናኘት እየሰራ ስላለው ስራ የባለድርሻ አካላት የጋራ ውይይት መድረክ ታህሳስ 8/2017 ዓ.ም በሮሪ ሆቴል ተካሂዷል::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚዳንት ተወካይና የኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አሰፋ ወርክሾፑን በይፋ ባስጀመሩበት ንግግራቸው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንደምርምር ዩኒቨርሲቲነቱ የመማር ማስተማርና የምርምር ስራዎችን ከማካሄድ ጎንለጎን የቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግር ስራዎች ላይ በጥልቀት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸው በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአካባቢው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር አዳዲስ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ዶ/ር ቴዎድሮስ አክለውም በሀገራችን አሳሳቢ እየሆኑ ከመጡ ችግሮች መካከል የስራ እድሉና የስራ ፍላጎት አለመጣጣም አንዱ በመሆኑ ይህንን ለመቅረፍ ከሚሰራው ደረጃ ዶት ኮም ጋር ስልጠናዎች በማዘጋጀት እንዲሁም ቀጥተኛ የስራ እድሎችን በማመቻቸት አመርቂ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የተማሪዎችና መምህራን ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ ደቻሳ ጉርማ ተማሪዎች ትምህርት መጨረሳቸው ብቻ ሳይሆን በተማሩበት ዘርፍ ለራሳቸውም ሆነ ለሀገራቸው የሚተርፉ ውጤታማ ዜጎች መሆን እንዲችሉ ከቀለም ትምህርት ባሻገር በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለስራ አለም ዝግጁ የሚያደርጓቸውን ክህሎቶች ተላብሰው እንዲወጡ እንደ ደረጃ ዶት ኮም የመሳሰሉ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የደረጃ ዶት ኮም ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ብርሃኑ ስለ ደረጃ ዶት ኮም አመሰራረትና ተግባሮች ገለጻ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በአፍሪካን ጆብስ ኔትወርክ (African jobs network) ስር ሆኖ በስራ ፈላጊና በቀጣሪ ድርጅቶች መካከል ድልድይ ሆኖ ለማገልገል እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም በይፋ መቋቋሙን እና ከበርካታ ተቋማት ጋር በመተባበር በስራ እድል ፈጠራ ላይ ተጨባጭ ስራ መስራቱን ገልጸዋል።

በመድረኩ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከተለያዪ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተወጣጡ ባለድርሻ አካላትየተሳተፉ ሲሆን የውይይቱ ዋና አላማ ከተለያየ ዘርፍ የተወጣጡ ቀጣሪ ድርጅቶች አዲስ ተመራቂ ተማሪዎችን ከመቅጠር አኳያ ምን ችግሮች እንደገጠሟቸው፣ የትኞቹ ክፍተቶች በተካሄዱ ስልጠናዎች እንደተሻሻሉ እንዲሁም ቀጣሪ ድርጅቶቹ ምን አይነት ክህሎቶችን እንደሚፈልጉ የጋራ መግባባት በመፍጠር የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን አቶ አሸናፊ አብራርተዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et