የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዋናው ግቢ ተማሪዎች ከደረጃ ዶት ኮም ጋር በመተባበር ተመራቂ ተማሪዎች በቀላሉ ከስራ አለም ጋር መቀላቀል የሚያስችላቸውን ክህሎት መገብየት የሚችሉበት የሙያ ማበልጸጊያ ክበብ (Career Club) ምስረታ መርሃግብር ታህሳስ 8/2017 ተካሂዷል::
በዚህ መርሃግብር ላይ የደረጃ ዶት ኮም ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና የክበቡ መስራች ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመቀጠር ምጣኔ ማጎልበቻና ሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ክብረት ፍቃዱ መልዕክት አስተላልፈዋል:: አቶ ክብረት የማዕከሉ ስራ ተማሪዎችን ማሰልጠን፣ ማማከርና ገበያ ማፈላለግ እንደሆነ ገልፀው ከስራው ስፋት አንጻር ለሁሉም ተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ ስላልተቻለ ስራውን ወደ ተማሪዎች ለማውረድ በማሰብ የሙያ ማበልጸጊያ ክበቡ እንዲቋቋም መደረጉን ተናግረዋል። ክለቡን ለማቋቋም ለአንድ ዓመት ያህል ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን የጠቆሙት አስተባባሪው አዲሱ ክለብ እስኪጠናከር በማዕከሉ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።
የደረጃ ዶት ኮም ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ብርሃኑ በበኩላቸው ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚያገኙትን ክህሎት ተጠቅመው የሀገራችን የልማት የትኩረት በሆኑት እንደ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ የማዕድን ሥራ፣ ማኑፋክቸሪንግና በሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው ገቢያቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። የክለቦች መቋቋም የስራ እድል ፈጠራ ተደራሽነቱን ለተማሪዎች የበለጠ ቅርብ ለማድረግ እንደሚያግዝ ታምኖ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በ18 የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ አሸናፊ ጨምረው ተናግረዋል።
የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጀመንት ትምህርት ክፍል አምስተኛ ዓመት ተማሪና የክበቡ ም/ፕሬዚዳንት የሆነችው ተማሪ ማህሌት ጌታቸው የክለቡን ምሰረታ በሚመለከት ማብራሪያ ስትሰጥ ክለቡ ተማሪዎች ክህሎቶቻቸውን እንዲያዳብሩና ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ እንደሚሰራ ገልጻለች::