የ "ሰላማዊ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ" ፕሮጀክት የማጠቃለያ መድረክ ተካሄደ።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የሰላም ተቋም ጋር ባለው "Life & peace institute" የተሰኘ የትብብር ፕሮጀክት አማካኝነት ስለሰላም ግንዛቤ ለመፍጠር ሲሰራቸው የነበሩ ክንውኖች ማጠቃለያ መድረክ ለሁለት ቀናት በአፍርካ ሕብረት አዳራሽና በመስክ መሰናዶዎች የታጀበ መርሃግብር አከናውኗል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሐ ጌታቸው መድረኩን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት ሰላም ለሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎቶች ከሚባሉት ዋነኛው በመሆኑ የሰላም መረጋገጥ የሰውን ልጆች ሌሎች ፍላጎቶች ሁሉ ለማሟላት መመለስ ያለበት የመጀመሪያው ጥያቄ መሆኑን አስገንዝበዋል። የዛሬ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም በመደበኛ ትምህርት ከሚያገኙት እውቀት ባሻገር በተለያዩ ግዜያት መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች በእንዲህ ዓይነት ውይይቶች የሚያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የግቢውንና የሀገሪቱን የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች የሚያነቁና ፖሊሲዎችን የሚቀርጹ መሪዎች እንደሚሆኑ በማሰብ ም/ፕሬዝዳንቱ የፕሮጀክቱን ሥራ አድንቀዋል::
የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አዳቶ በበኩላቸው ከጥቂት ዓመታት በፊት የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የጽንፈኛ አመለካከት የሚስተናገድባቸው የግጭት መነሻ ተቋማት ተደርገው ይወሰዱ እንደነበር አስታውሰው ይህን ለመቀየር ከኢትዮጵያ ሰላም ተቋም ጋር በመተባበር በተከታታይ በተሰራው ስራ አንጻራዊ መሻሻል ተገኝቷል ብለዋል። ሰላማዊ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ የመፍጠር አላማን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ፕሮጀክት ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ከተማሪው አንስቶ የአካዳሚክ ስታፉንና የአስተዳዳር አካላትን ተደራሽ ማድረጉን የጠቀሱት አቶ አየለ ሰላም በሁሉም ወገኖች የጋራ ትግል የሚጸና መሆኑን በማመን ሁሉም ወገን ከኔ ምን ይጠበቃል በሚል የኃላፊነት መንፈስ መመላለስ እንዳለበት አሳስበዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ እሰይ ጴጥሮስ የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑትንና በግዜ አጠቃቀም ምንነት እና ይህም ከሰላም ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ገለጻና ማብራሪያ የሰጡትን ዶ/ር ምህረት ደበበን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርስቲው አመራሮችን አመስግነው የዚህ ፕሮጀከት ዋነኛ ዓላማ ላለፉት 7 ወራት በዩኒቨርስቲው ሲተገበር የቆየዉ ፕሮጀክት መዝጊያን ማካሄድና ተማሪዎች ስለ ሰላም፣ የአይምሮ ጤንነት እንዲሁም ስለ ጊዜ አጠቃቀም ያላቸዉን አመለካከት ማዳበር መሆኑን ገልጸዋል።