የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ውሀ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሀገራችንን የውሀ ሀብት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን በአንድነት ለመስራት የሚያስችላቸውን የሥራ ውል ስምምነት ታህሳስ 21/2017 ዓ.ም ተፈራርመዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በፊርማቸው ወቅት እንደገለጹት ውሀ የሰው ልጆች ሁሉ መሰረታዊ ፍላጎት ከመሆኑ ባሻገር የሀገራችን ልዩ የተፈጥሮ ጸጋ በመሆኑ በአግባቡ አስተዳድሮ መጠቀም ይገባል። ኢትዮጵያ "የውሀ ማማ" ተብላ የምትጠራ ቢሆንም ባላት የውሀ ሀብት ልክ ተጠቃሚ ስላልሆነች ይህንን ለመቀየር በተቋማት መካከል በትብብር የሚሰሩ መሰል ሳይንሳዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው የገለፁት ፕሬዝዳንቱ የፕሮጀክቱን ስኬታማ አፈፃፀም ለማረጋገጥ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ዋ/ዳይሬክተር አቶ አጃነው ፈንታ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ሲሰራ ይህ የመጀመሪያው አለመሆኑን አስታውሰው ጥልቅ የውሀ ጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችንም በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በዚህ ስምምነት ሁሉንም ህብረተሰብ የንጹህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የእርሻና የኢንዱስትሪ ሴክተሩን ለማገዝ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በምርምር የመደገፍና ውጤታማ የማድረግ ስራ ይሰራልም ብለዋል።