በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከሲዳማ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ክልሎች ለተወጣጡ 160 የከተማ መሬትና ፕላን ባለሙያዎች ለ33 ቀናት ሲሰጥ የነበረውን ተግባር ተኮር ስልጠናና የምዘና ፕሮግራም አጠናቆ ታህሳስ 19/2017 ዓም አስመርቋል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የከተሞች አመሰራረት ከሰው ልጆች ግብርናን መሠረት ያደረገ የኑሮ ዘይቤ ጋር ተያይዞ የተጀመረና በሰው ልጆች ቁጥርና ፍላጎቶች መጨመር የተነሳ እየተስፋፋ የሄደ ጽንሰ ሀሳብ መሆኑን አስረድተዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም በሀገራችን የሚስተዋለውን ደረጃውን ባልጠበቀና በዘፈቀደ የሚመሰረተውን የከተሞች አወቃቀር ዘመናዊ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ በዓለም ላይ ያሉ የትልልቅ ከተሞችን ተሞክሮ በመውሰድ ከተሞቻችንን ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለማስቀመጥ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት የከተማ መሬት አስተዳደሩን በህግ አግባብ መምራት ይገባል ብለዋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ዚነት ኢብራሂም ስልጠናውን ያጠናቀቁ ባለሙያዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በከተማ መሬት አስተዳደር ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት በተለያየ ጊዜ ፕሮጀክቶች ቀርጾ ሙያተኞችን የማብቃት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል:: የመሬት አስተዳደር ሰራተኞች በይዞታ ቅኝትና ማጓደን፣ በይዞታ ምዝገባ ሲስተም፣ በከተማ ፕላኒንግና መሬት አስተዳደር እንዲሁም በንብረት ምዘና ላይ ያላቸውን እውቀት እንዲያሳድጉ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የወ/ገ/ደ/ተ/ሀ ኮሌጅ አካ/ጉ/ተ/ዲን ዶ/ር ሽመልስ ንጋቱ በበኩላቸው ለ33 ቀናት በኮሌጁ የተሰጠው በተግባር የታገዘ ስልጠና እያንዳንዱ ሰልጣኝ ወደስራ መደቡ ሲመለስ በሀገራችን ከፍተኛ ቅሬታ ከሚነሳባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ በሆነው የከተማ መሬት አስተዳደር ላይ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት እየተፋጠነ ያለውን የሀገራችንን እድገት የማስቀጠል ድርሻ እንዲወጡ ያስችላል ብለዋል።
በምረቃው ፕሮግራም ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቱና የክልል የዘርፉ ኃላፊዎች፣ የሀ/ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና የኮሌጁ ማህበረሰብ አካላት የተገኙ ሲሆን ስልጠናው ከአራቱም ክልሎች ለተወጣጡ 128 ወንድና 32 ሴት በጠቅላላው ለ160 ባለሙያዎች የተሰጠ መሆኑ ተገልፅዋል:: በማጠቃለያውም ለአሰልጣኝ መምህራንና ለተመራቂ ባለሙያዎች የእውቅናና የሙያ ምዘና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።