ኮሌጁ ለት/ክፍል ሀላፊዎችና ለተማሪ አማካሪ መምህራን የአቅም ግንባታ ሰልጠና ሰጠ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በስሩ ለሚገኙ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና የተማሪ አማካሪ መምህራን በዩንቨርሲቲው መተዳደሪያ ህግና ደንብ (ሌጅስሌሽን) አረዳድ እንዲሁም ከሬጅስትራር አሰራር ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል::

የተ/ቀ/ሳ/ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዙፋን በደዊ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በኮሌጅ ደረጃ በተደጋጋሚ ከሚቀርቡ ቅሬታዎች መካከል የተማሪዎች ውጤት በአግባቡ አለመያዝና አለመተላለፍ አንዱ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ባለሙያው ተገቢውን ግንዛቤ ሊጨብጥ እንደሚገባው ገልፀዋል። ዶ/ር ዙፋን አክለውም በአሁኑ ወቅት በኮሌጁ ስር የሚገኙ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የዲፓርትመንት ኃላፊዎች አዳዲስ አባላት እንደመሆናቸው የዩኒቨርሲቲውን ህግና የሬጅስትራር ህጎችና አሰራሮች ላይ የሚገጥማቸውን የግንዛቤ ክፍተት ለመቅረፍ የአዲሱ አመት የትምህርት ጊዜ በተጀመረበት በዚህ ጊዜ ስልጠናውን መውሰዳቸው ለስራቸው ስኬታማነት የጎላ ጥቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የኮሌጁ አካዳሚክ ጉዳዮች ተ/ዲን ዶ/ር ይፋት ደምባርጋ በበኩላቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ የመጨረሻ ግብ ተማሪው የሚገባውንና የራሱ የሆነውን ውጤት አግኝቶ ትምህርቱን እንዲያጠናቅቅ ማድረግ በመሆኑ በዚህ ሂደት ውስጥ ሊገጥሙ የሚችሉ ስህተቶችን ለመቀነስ በየደረጃው የሚገኝ ሰራተኛ ተገቢውን ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል። የሬጅስትራር ስራ ከምዝገባ ጀምሮ እስከ ትምህርት ማጠናቀቂያ ጊዜ ድረስ ያለውን ሂደት የሚያጠቃልል በመሆኑ ነገሮች ተደራርበው ኮሌጁ ድረስ ከመምጣታቸው በፊት የተቀመጠውን አሰራር በመከተል በዲፓርትመንት ደረጃ መልስ መስጠት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ዶ/ር ይፋት ጨምረው ገልጸዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et