የኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ሃብት ልማት: ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ታህሳስ 3/2017 ዓም የመግቢያ ውይይት አድርጓል::
የቋሚ ኮሚቴው የትምህርት ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ አስተባባሪ ክቡር አቶ ታደሰ ጌጡ የመግቢያ ውይይቱን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት ምክር ቤቱ በዋናነት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በአካል ተገኝቶ ክትትል: ቁጥጥርና ድጋፍ በማድረግ ተቋማት ለተሰጣቸው ኃላፊነት ብቁ መሆናቸውን ያያል ብለዋል:: በመሆኑም ከዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ አንፃር የመማር ማስተማር: የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ እየሰራው ያለው ከሚጠበቀው አንፃር ምን እንደሚመስል: የመልካም አስተዳደር ይዞታው: የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ የመሳሰሉትን እናያለን ሲሉ የምልከታ መርሃግብሩን ይፋ አድርገዋል:: ከዚህ በተጨማሪም ከዩኒቨርሲቲው ልየታና የራስገዝነት ጉዞ ዝግጅት አንፃር ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ: አለማቀፋዊነት ላይ ምን እንደተሰራና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ከባቢ ለመፍጠር የተሰሩ ሥራዎች ምን እንደሚመስሉ በተቻለ መጠን በአካል ጉብኝት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሚደረጉ ውይይቶች እንደሚገመግሙ አብራርተዋል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በበኩላቸው የቋሚ ኮሚቴውን አባላት እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኃላ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሰባት በጣም ሰፋፊ ካምፓሶች ያሉት ትልቅና አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን አስረድተዋል:: በእነዚህ ግቢዎች ሁሉ ራሱን የቻለ የፋይናንስና አስተዳደር መዋቅር እንዳለ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ አሁን ካለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንደ መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን ሀብት አሰባስቦ ራስገዝ ለመሆን ከሚደረገው ጥረት አንፃር የዩኒቨርሲቲው ስፋትና ይዞታ በራሱ ከፍተኛ ጥንቃቄና ሥራ የሚፈልግ መሆኑን አንስተዋል:: በተጨማሪም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና የተማሪዎች አገልግሎት ላይ የምግብ አቅርቦትን ጨምሮ የተሻለ ጥራት እንዲኖረው ብዙ ዋጋ ተከፍሎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ኮሚቴው ጠንካራ ጎን ብቻ ሳይሆን መሻሻል ያለበትንም ሥራ አይቶ እንዲያመላክተን ብሎም የሚያስፈልገውን መንግስታዊ ድጋፍ እንደሚያደርግልን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል::