የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ድህረምረቃ ትምህርት ቤት ከቤልጂየሙ IQ-GEAR (Inter-university collaboration for education and research) ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የሚሰሯቸውን ምርምሮች ደረጃ ለማሳደግ ለአማካሪ ፕሮፌሰሮችና ተባባሪ ፕሮፌሰሮች ስልጠና ሰጥቷል።
የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዲን ዶ/ር ታዬ ገ/ማሪያም ስለ ስልጠናው ጠቀሜታ ሲያስረዱ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በየወቅቱ የሚሰሩ የምርምር ስራዎች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ አማካሪዎችን ብቃት ማሳደግ ይገባል ብለዋል። ይህ ስልጠና በአይነቱ የመጀመሪያ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ታዬ ከዚህ በፊት የአሰልጣኞች ስልጠና በወሰዱ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን አሰልጣኞች በሶስት ዙሮች ተከፍሎ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ከአሰልጣኞቹ አንዱ በሀ/ዩ የፖሊሲና ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ባልደረባ ዶ/ር መልሰው ደጀኔ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር ስራ ያለበትን ክፍተት ለመለየት በተሰራው ጥናት ከተመላከቱት ግኝቶች መካከል አማካሪዎች ተማሪዎችን የሚያማክሩበት መንገድ ላይ የታየው ክፍተት ዋነኛው በመሆኑ ይህንን ክፍተት ለማጥበብ መሰል ተከታታይ ስልጠናዎችን ለመስጠት መወሰኑን ተናግረዋል። በሀገሪቱ ከሚገኙ የመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ 16 የሚጠጉ ፕሮፌሰሮችና ተባባሪ ፕሮፌሰሮች ሰልጥነው እውቅና በማግኘት መሰል ስልጠናዎችን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ላይ እየሰጡ እንደሚገኙ ዶ/ር መልሰው አክለዋል።
ሌላው አሰልጣኝ በግብርና ኮሌጅ የስነ-ምግብ፣ ምግብ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ት/ቤት ባልደረባ ዶ/ር ብሩክ ብርሃኑ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የማማከር ስራውን ሳይንሳዊና ውጤታማ ማድረግ የሚሰሩ የምርምር ስራዎችን ደረጃ ከማሳደግና ተወዳዳሪ ከማድረግ ባሻገር ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ ጥቅምን እንደሚያስገኝ እምነታቸውን ተናግረዋል።