ቋሚ ኮሚቴው የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ሥራዎች ተዘዋውሮ ጎበኘ::
በኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ስራዎችን ከህዳር 7-8/2017 ዓም በየካምፓሱ በአካል ተገኝቶ ጎብኝቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢና የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በጉብኝቱ ወቅት ቋሚ ኮሚቴው ኢንተርፕራይዙ የነበረበትን የኦዲት ግኝት አስመልክቶ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።
በዚሁ መሠረት ኢንተርፕራይዙ መውሰድ ያለበትን ማሻሻያዎች ተግባራዊ በማድረግ ተቋሙ የታለመለትን ዓላማ ለማሳካት ደንብና መመሪያን ተከትሎ በመስራት የራሱን ገቢ ማመንጨት እና የተሻለ ስራ በመስራት የዩኒቨርስቲውን የውስጥ አቅም ሊያሳድግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ማሻሻያውን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ ማሻሻያ ያልተደረገባቸው ግኝቶችን ለመፍታት የተዘጋጀ የአሰራር ስርዓት ስለመኖሩ ቋሚ ኮሚቴው በጉብኝቱ ወቅት ካነሳው ውስጥ የሚጠቀስ ነው።
ቋሚ ኮሚቴው በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ እና በሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ ዕደ ጥበብ ማዕከላት እንዲሁም በዋናው ግቢ የሚገኙ የገቢ ማመንጫ ስራዎችን አሁናዊ ይዞታ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።