ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ4,500 በላይ የሚሆኑ የ2017 ዓም አዲስ ገቢ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎቹን ከዛሬ ጀምሮ እየተቀበለ ነው::
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ህብረት ከተማሪዎች አገልግሎት ዲን ፅ/ቤት እንዲሁም ከካምፓስ ፀጥታና ደህንነት አካላት ጋር በመቀናጀት ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል እያደረጉ ነው::
የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ከጸጥታና ደህንነት እንዲሁም ከምግብና መኝታ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ሰፊ ዝግጅት በዩኒቨርሲቲው ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸው ተማሪዎቹ በዋናው ግቢና በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንደተመደቡ ተናግረዋል:: ም/ፕሬዝዳንቱ ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲው ይዘው የመጡ ወላጆችም ሆነ ተማሪዎች ያለምንም ስጋት በአቀባበል ኮሚቴው አባላት የሚሰጣቸውን መመሪያ በመከተል አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ለተማሪዎቹም እንኳን ደህና መጣችሁልን ብለዋል::
የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተማሪዎች አገልግሎት ም/ዲን መ/ር ዳሞት ተስፋዬ በበኩላቸው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የብዙ አዳዲስ ተማሪዎች የቅድሚያ ምርጫ ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንደመሆኑ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን አጠቃላይ የተማሪዎች አገልግሎቱና የካምፓስ ቆይታው የተሻለና ሰላማዊ እንዲሆን በትጋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ሀሳባቸውን የሰጡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከመምጣታቸው በፊት የቀድሞ ተማሪዎችን መረጃ መጠየቃቸውን ገልጸው ጥሩ ግብረ መልስ በማግኘታቸው ዩኒቨርሲቲውን መርጠው መምጣታቸውን ተናግረዋል:: እስከአሁን ያለው አቀባበልም አስደሳች ሆኖ እንዳገኙት ገልፀዋል።
አዲስ የዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች እንኳን ወደ ልህቀት ማዕከሉ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንኳን ደህና መጣችሁ እያልን መልካም የትምህርትና የስኬት ዘመን እንዲሆንላችሁ ከልብ እንመኛለን!