አለምዓቀፉን የኢንተርፕሩነርሽፕ ሳምንት በማስመልከት ለተመራቂ ተማሪዎች ስልጠና ተሰጠ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ጽ/ቤት ከኢንተርፕሩነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከህዳር 9-15/2017 የሚከበረውን አለምዓቀፍ የኢንተርፕሩነርሺፕ ሳምንት ምክንያት በማድረግ ለወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች የስራ እድል ፈጠራ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።

የወ/ገ/ደ/ተ/ሀ/ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ተሻለ ወ/አማኑኤል ስለስልጠናው አስፈላጊነት ሲናገሩ ዩኒቨርሲቲው በሰራው የዳሰሳ ጥናት ከሚያስመርቃቸው ተማሪዎች መካከል 40% የሚሆኑት ምሩቃን ብቻ ተቀጥረው ወደ ስራ የሚገቡ መሆኑን ጠቁመው የቀሩት አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ተመራቂዎች ደግሞ የራሳቸውን ስራ ከመፍጠር ይልቅ ስራ በማፈላለግ እንደሚደክሙ ገልጸዋል።ዲኑ ይህንን ተቀጥሮ በመስራት ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነን አመለካከት በማስቀረት ተመራቂዎች የራሳቸውን ስራ መፍጠር እንዲችሉ የስራ ፈጠራ ግንዛቤን ማሳደግና ወደ ትግበራ መግባት የሚችሉበትን ቁልፍ ከስልጠናው ያገኛሉ ብለዋል።

የሀ/ዩ ኢንተርፕሬነርሺፕ ልማት ማዕከል አስተባባሪ ኢ/ር ትዕግስት አሰፋ በበኩላቸው በዓሉ በአለምአቀፍ ደረጃ ለ15ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ የሚከበር መሆኑን ገልጸው በዚህ ወቅት ለሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ተስማሚ የሆኑና ሊተገበሩ የሚችሉ ስኬታማ የስራ ፈጠራ ልምዶችን በማጋራት 130 የሚሆኑ የኮሌጁን ተመራቂ ተማሪዎች የማነሳሳት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ስራ ፈጠራ ሩቅና በአነስተኛ በጀት ሊተገበር የማይችል ተደረጎ የሚታሰበውን አመለካከት በመቀየር ተማሪዎች በአካባቢ ከሚታይ ችግር ውስጥ መፍትሔ በማመንጨት ተጠቃሚ መሆን የሚያስችሉ ክህሎቶችን እንዲላበሱ ማስቻል በሀገርአቀፍ ደረጃ የሚታየውን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ አይነተኛ መፍትሔ መሆኑንም አስተባባሪዋ ጨምረው ገልጸዋል።

ተመራቂ ተማሪዎቹ ከስልጠናው በኋላ በሰጡት ግብረመልስ የትኛውንም ስራ ለመስራት ሀሳብ የመጀመሪያውና ትልቁ መሳሪያ መሆኑን መረዳታቸውን እና ትምህርታቸውን በሚያጠናቁቁበት ወቅት በግልና በጋራ ሆነው የራሳቸውን ስራ ለመፍጠር በከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ እንደሚገኙ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et