የአፈር አሲዳማነት ለመቀነስ በተሰሩ የምርምር ስራዎች ላይ የመስክ ምልከታ ተካሄደ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኢት-ባዮቻር ፕሮጀክት በሲዳማ ክልል ሁላ ወረዳ ሀንቆ ሞሊቻና ሉዳ ቀበሌዎች በሚገኙ አስር የአርሶአደር ማሳዎች ላይ የአፈር አሲዳማነትን በማከም የበቆሎና ስንዴ ሰብል ምርታማነት ለማሳደግና አርሶአደሩን ለማላመድ ምርምር እያካሄደ ያለበትን የሙከራ ጣቢያ የመስክ ምልከታ ህዳር 6/2017 አካሂዷል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ፍሰሀ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት በሀገራችን ከሚገኘው የሚታረስ መሬት 40% ያህሉ አሲዳማ ባህሪ የሚታይበት መሆኑን ጠቁመው በተለይም በደጋማ አካባቢዎች አሲዳማነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይህንን ችግርና የሚያስከትለውን የምርት መቀነስ መፍትሔ ለመስጠት ባዮቻር የተባለ አፈርን የሚያክም ለማዳበሪያ ተስማሚ የሆነ ምርት በማዘጋጀት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እያስተዋወቁና እያላመዱ እንደሚገኙም አቶ ማርቆስ ተናግረዋል።

የETH-የአፈር ባዮቻር ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ሽመልስ ግዛቸው በበኩላቸው ፕሮጀክቱ EBFZ በተባለ የጀርመን ተቋም የሚረዳ መሆኑን እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከሌሎች ሶስት የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። አስተባባሪው ጨምረውም የመስክ ምልከታው የአፈር አሲዳማነትን ለማከም ከቡና ገለባ ተረፈ ምርት የተዘጋጀውን ባዮቻር እንዴት ከተፈጥሮ እንዲሁም ሰው ሰራሽ የእርሻ ማዳበሪያዎች ጋር በማጣመር በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን የበቆሎና የስንዴ ሰብል ምርታማነት ማሳደግ ይቻላል በሚለው ዙሪያ ግንዛቤ ይፈጥራል ብለዋል።

የሁላ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽ/ቤት የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ልማሳ ሪኪዋ በአካባቢው ካለው አሲዳማ የአፈር ባህሪ የተነሳ የአርሶአደሩ ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰው ቀደም ሲል ችግሩን ለመፍታት ኖራን በመጠቀም አፈሩን የማከም ስራ ቢሰራም ኖራ ውድ በመሆኑ ውጤት እንዳላስገኘ ተናግረዋል። ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እያስተዋወቀ ያለው ባዮቻር በተወሰኑ የእርሻ ማሳዎች ላይ ተሞክሮ የተሻለ ምርት ማስገኘት መቻሉን የገለጹት አቶ ልማሳ አርሶአደሩ ይህንን ምርት ለመጠቀም ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዳሳየም ገልጸዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et