ለቀዶ ህክምና ስፔሻሊቲ ሀኪሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የቀዶ ህክምና ዘዴዎች ላይ  ስልጠና ተሰጠ::

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ለቀዶ ህክምና ስፔሻሊቲ ሰልጣኝ ሀኪሞች የተለያዩ የእንስሳት አካላትን በመጠቀም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የቀዶ ህክምና አሰጣጥ ዘዴዎች ላይ የተግባር ስልጠና ተሰጥቷል።

የሆስፒታሉ የክሊኒካልና አካዳሚክ ጉዳዮች ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ክብሩ ክፍሌ እንደገለጹት የስልጠናው ዋነኛ ዓላማ በዩኒቨርሲቲው በመማር ላይ ያሉት የቀዶ ህክምና ስፔሻሊቲ ሰልጣኝ ሀኪሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ አቅም ለመፍጠር ነው።

ከተለያዩ የአውሮፖ ሀገራት ከተወጣጡና ዩሮ-ሊንክ ተብሎ ከሚታወቀዉ በጎ ፈቃደኛ የስፔሻሊቲ ሀኪሞች ቡድን ጋር በመተባበር ለአንድ ሳምንት በተለያዩ ዘመናዊ የቀዶ ህክምና ዘዴዎች ላይ  ስልጠናው መሰጠቱን ያስረዱት ዶ/ር ክብሩ በተለይም በኩላሊት ጠጠር ዘመናዊ የቀዶ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ልዩ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።

በሆስፒታሉ የኩላሊት ህክምና ክፍል ኃላፊው ዶ/ር ጥላነህ ልይህ በበኩላቸው ዩሮ-ሊንክ የስፔሻሊቲ በጎ ፈቃደኛ ሀኪሞች ቡድን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በነበረው የረዥም ጊዜ የትብብር ስምምነት የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። ዶ/ር ጥላነህ በሰጡት ማብራሪያ በተለይም የኩላሊት ጠጠር ታካሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የህክምና መጠባበቂያ ቀጠሮ ለመቀነስ የሚረዳ በዩሮ-ሊንክ አማካይነት በእርዳታ የተገኘው ዘመናዊ የኩላሊት  ጠጠር ቀዶ ህክምና ማሽን (PCNL) አገልግሎት  በመስጠት ላይ እንደሚገኝ  አስረድተዋል። አዲሱ የኩላሊት ጠጠር ዘመናዊ የቀዶ ህክምና ማሽን በተገጠመለት ዲጅታል ካሜራ ተጠቅሞ ጠጠሮቹን በመሰባበርና በማድቀቅ በሽንት መልክ እንዲወጡ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ  የታካሚዎችን ገንዘብና ጊዜ የሚቆጥብ መሆኑን   ከዶ/ር ጥላነህ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

የዩሮ-ሊንክ በጎ ፈቀደኛ ስፔሻሊቲ ሀኪሞች ቡድን አስተባባሪ ዶ/ር ግርሐም ዋትሰን በበኩላቸው ላለፉት 54 ዓመታት በኢትዮጵያ ሁሉም አከባቢዎች በመዘዋወር የነፃ ህክምና አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልፀው በአሁኑ ወቅት በህክምናው ዘርፍ ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ኢትዮጵያዊያን ሀኪሞች ተረድተው ሕዝባቸውን እንድያገለግሉ የዕውቅት ሽግግር ለመፍጠር   እየሠሩ  መሆኑን  አስረድተዋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et