የቦሳድ (BOSAD) የምርምር ውጤትን መሰረት ያደረገ ስልጠና ተሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ትምህርት ክፍል ከኢትዮጵያ የአጥንት ሐኪሞች ማህበር (ESOT) ጋር በመተባበር ከሲዳማ ክልል ለተውጣጡ ወጌሻዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና የትምህርት ቤት ማህበረሰብ ክፍሎች የቦሳድ ጥናት ውጤትን መሰረት ያደረገ የሶስት ቀናት የስልጠናና ምክክር መድረክ በኦሲስ ሆቴል አዘጋጅቷል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሻሊስት እና የጀርባ አከርካሪ ሕክምና ሰብ-ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ዶ/ር መንግስቱ ገ/ ዮሃንስ እንደገለፁት ቦሳድ (BOSAD) ማለት ሃገር አቀፍ የሆነ የጥናት እና ምርምር ቡድን ሲሆን ስሙም BOne Setting Associated Disability ከሚል የተወሰደ መሆኑን ገልፀው ጥናቱ እንዲሰራ ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ከባህላዊ የአጥንትና መገጣጠሚያ ህክምና ጋር ተያይዞ የሚስተዋለዉ የጎንዮሽ ጉዳት ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱ መሆኑን ጠቁመዋል። እነዚህ በየዕለቱ የሚስተዋሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሙሉ በሙሉ መከላከል የሚቻል ከቋሚ የአካል ጉዳተኝነት እስከ ሞት የሚያደርሱ የተለያዩ ከፍተኛ ውስብስብ የጤና ችግሮች መሆናቸዉን ዶክተሩ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር መንግስቱ እንደተናገሩት የጥናቱ ውጤት በህፃናት ላይ የሚስተዋለዉ የጎንዮሽ ጉዳት ከአዋቂዎች አንፃር እጅግ ከፍተኛና ዉስብስብ መሆኑን፣ ህፃናት በብዛት የሚጎዱት ደግሞ በት/ቤት አካባቢ በመውደቅ መሆኑን እና በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ብሎም ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸውን አብራርተዋል። የምክክርና ስልጠናውን መድረክ ዓላማ ሲያስረዱም "ሰዎች የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳት ደርሶባቸው በባህላዊ መንገድ ከታከሙ በኃላ የሚከሰቱ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመቀነስ የሚረዳ ሲሆን በዚህም ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ዘመኑ በደረሰበት የእዉቀት ደረጃ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ፣ ተደራሽ የሆነ፣ ብሎም አቅምን ባገናዘበ መልኩ የሚሰጥ የአጥንትና መገጣጠሚያ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል" መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ሰልጣኞች ከስልጠናው ባገኙት የግንዛቤ ማስጨበጫ በመጠቀም ታካሚዎች ያጋጠማቸውን ችግር በትክክል በመለየት፣ ትክክለኛውን ህክምና በተገቢው ሰዓት እንዲሰጡ፣ ባህላዊ ህክምና የሚሰጡ አካላትም አቅማቸዉ የሚፈቅደዉን ብቻ እርዳታ በማድረግ በተለይም አጥብቆ ባለማሰር እና በተደጋጋሚ ባለማሸት ሊከሰቱ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደሚችሉ ሐኪሙ ገልፀዋል። "ክፍት ስብራት፣ መገጣጠሚያ አካባቢ ያለ ስብራት እና የህፃናት አጥንት ጉዳት በቀላሉ ላልተፈለገ ዉስብስብ የጤና እክል ስለሚዳረግ ችግሩ ያጋጠማቸው ሰዎች በጤና ተቋማት ብቻ በመቅረብ በአግባቡ እንዲመረመሩና አገልግሎት እንዲያገኙ ይመከራል:" ሲሉ ዶ/ር መንግስቱ አሳስበዋል።