የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል የ2017 በጀት ዓመት አንደኛው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የገመገመበት መድረክ ህዳር 3/2017 ዓም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ አካሂዷል::
የዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ መድረኩን ባስጀመሩበት ንግግራቸው ዘንድሮ የግምገማ መድረኩን ለየት የሚያደርገው በቅርቡ በማኔጅመንት ውሳኔ ካውንስሉ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በነበረው የአባላት ስብጥር ላይ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችን ማካተቱ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ሩብ ዓመት ግዜ ውስጥ በየኮሌጆችና ትምህርት ክፍሎች ደረጃ ምን ታቅዶ ምን እንደተከናወነ እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና በቀጣይ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቅጣጫ ለመያዝ መድረኩ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተ/ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።
በግምገማ መድረኩ ከስምንት ኮሌጆች: የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና በንሳ ዳዬ ካምፓስ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ካውንስሉ በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል::
ውይይቱን የመሩት ሶስቱም ምክትል ፕሬዝዳንቶች ዩኒቨርሲቲው አሁን በሚጠበቅበት የራስገዝነት እና የምርምር ዩኒቨርሲቲ የመሆን የሽግግር ወቅት ላይ እንደመሆኑ በየዘርፋቸው በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ያላቸውን ግብረመልስ ሲሰጡ አስሩም የዩኒቨርሲቲው ቅርንጫፎች በቀሪዎቹ የዓመቱ ወራት ውስጥ በአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው መፃኢ ዕድል ላይ ወሳኝ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል::
በአካዳሚክ ዘርፍ ላይ ድጅታላይዜሽን: የድህረምረቃ ፕሮግራሞችን ማጠናከር: የፕሮግራሞች ክለሳና አለማቀፍ እውቅና ማግኘት: ፕሮግራሞችን ከዩኒቨርሲቲው ልዩ የትኩረት መስክ ጋር ማጣጣም: ቤተሙከራዎችንና ቤተመፃህፍትን በቴክኖሎጂ ግብዓቶች ማሳደግ እንዲሁም የተማሪዎች ተግባር-ተኮር ትምህርትና ክህሎት ማሻሻያ እድሎች ላይ የበለጠ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ም/ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ኢ/ር ፍስሃ ጌታቸው ተናግረዋል::
በተመሳሳይ በምርምር: የማህበረሰብ አገልግሎትና ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዘርፎች ላይ የበለጠ መስራት የሚጠበቀው በጭብጥ-ተኮር ምርምሮችና የድህረምረቃ ተማሪዎችን ያካተቱ ፕሮጀክቶች ላይ ማትኮር: በዓለምአቀፍ ጆርናሎች ላይ ያለውን ህትመት መጨመር: የተጀመሩ ጆርናሎችን እውቅና እንዲያገኙ ማጠናከር: ራስን ለመቻል የሚረዱ ጠንካራ የትብብር ፕሮጀክቶችን ማምጣት: ከኢንዱስትሪው ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠር: የምርምርና ልህቀት ማዕከላትን ማዘመንና አለማቀፍ ስታንዳርድ ማሰጠት: ከማህበረሰቡ ጋር ትርጉም ያለው ትስስርና ትብብር መፍጠር: ያለንን ተፈጥሯዊና አካባቢያዊ ፀጋ ለይቶ ፈጠራ የታከለበት ችግር ፈቺ ምርምር መስራት እንደሚገኙበት ም/ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ ገልፀዋል::
በመጨረሻም በአስተዳደርና ልማት ዘርፉ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው በሰው ኃይልና የመሰረተ ልማት አቅም ግንባታ ላይ ሆኖ ከዚህ በኃላ እንደበፊቱ ወደጎን መስፋት ሳይሆን ጥራትና አግባብነት ላይ የበለጠ እንደሚሰራ: ካለው የበጀትና የገበያ ሁኔታ ጋር የተናበበ ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገባቸው ጉዳዮች ልየታ ላይ የተመሰረተ የግዥ: የጥገናና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ሥራዎች ላይ ብሎም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ተጠቅሞ አገልግሎቶችን በሙሉ አውቶሜት ማድረግ ላይ መሆኑን ም/ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ አብራርተዋል::