የአኩሪ አተርና ቦለቄ ሰብሎች ምርታማነት በማስፋት ላይ የባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታና ውይይት ተካሄደ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና በኔዘርላንድ መንግስት ትብብር የሚደገፈው የRAISE-FS ፕሮጀክት በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ዙርያ ወረዳ በአርሶአደሩ ማሳ ላይ እየተገበረው የሚገኘውን የአኩሪ አተርና ቦለቄ ምርት የማላመድና የማስፋት የምርምር ስራ ውጤት ለመገምገምና ልምዱን በቀጣይነት ለማስፋት ያለመ የባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታና ውይይት ጥቅምት 30/2017 ዓም በዶሬ ቀበሌ አካሂዷል::

ተ/ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በመስክ ምልከታው ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በሽግግር ላይ ያለው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሀገራዊው የልማት እቅድ ጋር የተጣጣሙ የምርምር ስራዎችን ከመስራትና የህብረተሰቡን ሕይወት ከማሻሻል አኳያ ዋነኛ የትኩረት መስክ በሆነው በግብርና ዘርፍ ላይ አርሶአደሩንና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተገበረ እንደሚገኝ ገልፀው በቀጣይም ከአካባቢው አስተዳደርና ከአርሶአደሩ እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር አካላት ጋር በዘለቄታው ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ብለዋል።

የም/ቴ/ሽ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ በበኩላቸው የRAISE-FS ፕሮጀክት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚሰራቸው የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች መካከል በስነምግብ ከፍተኛ ፕሮቲን ያላቸውን አኩሪ አተርና ቦለቄ ሰብሎች በአርሶአደሩ ማሳ ላይ ከማላመድ ባሻገር የገበያ ሰንሰለት ትስስሩን በማጠናከር በክልሉ ከሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ለማስተሳሰር የሄደበት ርቀት እጅግ ያስመሰግነዋል ብለዋል::

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የRAISE-FS ፕሮጀክት አስተባባሪው ዶ/ር ቴዎድሮስ አያሌው ስለ ፕሮግራሙ ባደረጉት ገለፃ ፕሮጀክቱ የሀገራችንን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ዋና ትኩረቱ አድርጎ አካታች የሆነና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርጉ በምርምር የታገዙ ምርጥ የሰብል አይነቶችን አዋጭነትና ተስማሚነት በማጥናት: በማላመድና በማስፋት ብሎም የግብርና ባለሙያዎችንና አርሶ አደሮችን በአመራረትና የምግብ አዘገጃጀት ጭምር በማሰልጠን አቅማቸውን የማሳደግ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የጉብኝቱ ዓላማ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተወያይተው ውጤቱን ለማስቀጠል እንዲችሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዕለቱ የተጋበዙት ባለድርሻ አካላት ከመንግስት በግብርናው ዘርፍ ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች: በፕሮጀክቱ የታቀፉ ሞዴል አርሶአደሮች: የግብርና ልማት ባለሙያዎች: የግብርና ምርምርና ምርጥ ዘር አቅራቢ ተቋማት: አጋር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የዩኒቨርሲቲው አመራርና ተመራማሪዎች ሲሆኑ በውይይቱ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡ አርሶአደሮች እየተደረገላቸው በሚገኘው ድጋፍና ክትትል በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው በተለይ ለአካባቢው አዲስ ከሆነው የአኩሪ አተር ሰብል ጋር መላመዳቸውንና በቅርቡ የሚደርስ ምርት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የሀዋሳ ዙርያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ሳቶ ይስሐቅ ባደረጉት ንግግር ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ብዙ በምርምር የታገዙ ድጋፎች እየደረገ በመሆኑ በሕዝቡና በፅ/ቤታቸው ስም ልባዊ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ያስተዋወቀውን የአኩሪ አተርና ቦለቄ ሰብሎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስፋፋትና የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ቢሮው በትጋት እንደሚሰራ ገልፀዋል::

Facebook (https://www.facebook.com/Hawassa.University?mibextid=ZbWKwL)

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et