በሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ የምር/ቴ/ሽ/ም/ፕ/ጽ/ቤት ስር የሚሰራው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ሥራዎቹን ለማጠናከር ያለመ የባለድርሻ አካላት የምክክር አዉደጥናት ጥቅምት 23/2017 ዓም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ አካሂዷል።
የም/ቴ/ሽ/ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸዉ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት እንደስራ ክፍል ከተመሰረተበት ጀምሮ ላለፉት 13 ዓመታት በተመረጡ 6 ዘርፎች ማለትም በሰብል ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በጤና እና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዘርፎች ከ6 የቴክኖሎጂ መንደሮች አንስቶ በአሁኑ ሰዓት በ19 ወረዳዎች የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎቹን ማስፋቱን ገልፀዋል። ም/ፕሬዝዳንቱ የመድረኩ ዓላማ እስካሁን ምን እንደተሰራ እና ምን መጠናከር እንዳለበት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት አገልግሎቱን በጋራ አጠናክሮ ለመቀጠል መሆኑን ተናግረዋል።
ተ/ፕሬዝዳንት ክቡር ችሮታዉ አየለ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲዉ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎቹ ለሀገር እድገት ብሎም ለአካባቢው ማህበረሰብ እስካሁን የቻለውን በጎ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንዳለ ጠቅሰው በተለምዶ የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ካለው ሰፊ የግንዛቤ ማነስ የተነሳ የሚጠበቀውን ያህል ርቀት አለመጓዙን ተናግረዋል:: ዶ/ር ችሮታው በንግግራቸው "የማህበረሰብ አገልግሎት ሲባል ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው ማህበረሰብ ደግሞ ዝም ብሎ የሚቀበለው አገልግሎት ሳይሆን ሁለቱም በአጋርነት ስሜት የማህበረሰቡን ችግር በሳይንሳዊ እውቀት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ የሚያፈላልጉበት ትብብር" መሆኑን አስምረውበታል:: እስካሁን በተለምዶ ዩኒቨርሲቲው ወደ ማህበረሰቡ በመቅረብ ይሄንን ችግር በጥናት ስለደረስንበት እንፍታው ማለት ብቻ እንደማይበቃ የጠቀሱት ተ/ፕሬዝዳንቱ የማህበረሰብ መሪዎችም ወደ ዩኒቨርሲቲው ቀርበው የቸገራቸውን ጉዳይ አብሮ ለመፍታት የሚተባበሩበት አሰራር መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል:: በዚህም ዩኒቨርሲቲው ከማህበረሰቡ አመራር ጋር የልማት አጋር መሆኑን በመረዳት ዩኒቨርሲቲዉ በጥሩ ሁኔታ እንዲያገለግል እና የህብረተሰቡን ፍላጎትና ችግር ገብቶት እንዲያግዝ አጋርነታችን እንዲጠናከር መሰል የምክክር መድረኮች ቢያንስ በዓመት ሁለት ግዜ ይኖረናል ብለዋል።
የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ፍስሐ ላለፉት ሦስት ዓመታት በዳይሬክቶረቱ የተሰሩ ስራዎች ሪፖርት እንዲሁም የ2017 ዓ.ም የክንውን ዕቅድ ለተሳታፊዎች ካቀረቡ በኃላ በቀረበው ገለፃ ላይ ግብረመልስ እና ውይይት ተደርግጓል::
በባለድርሻ ውይይት መድረኩ ላይ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልል ሁሉም ክላስተር ቢሮዎች፣ ከ4ቱም ዞኖች፣ ከ26 ወረዳዎች እና ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ሁሉም መምሪያዎች የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የተጋበዙ ሲሆን በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዉ ፕሮግራሙ ተጠናቋል።