የድህረምረቃ ትምህርት ባጋጠሙት ተግዳሮቶች መፍትሔ ላይ ውይይት ተካሄደ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ድህረምረቃ ት/ቤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣውን የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ተማሪዎች ቁጥር ለማሻሻልና ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 16/2017 አካሂዷል::

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲኖች፣ ተባባሪ ዲኖች፣ የድህረምረቃ ት/ቤት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ምሁራን ተሳታፊ በሆኑበት የውይይት መድረክ ላይ ተ/ፕሬዚደንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በርከት ያሉ የምርምር ስራዎች የሚሰራባቸውን የድህረምረቃ ትምህርት ዘርፎች በስፋት አጠናክሮ የመሄድና የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል:: ተ/ፕሬዝዳንቱ በድህረምረቃ ፕሮግራሞች ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮችን ሀገርአቀፍ እና ተቋም-ተኮር ብሎ በመለየት በየደረጃው ችግሮቹን እየፈቱ መሄድ ይገባል ሲሉም አክለዋል።

የአካ/ጉ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሐ ጌታቸው በበኩላቸው በውይይቱ የወደፊቱ የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት አሰራር ምን መምሰል ይገባዋል የሚለውን አቅጣጫ ለማስቀመጥ ውስጣዊና ውጫዊ ተብለው የተለዩ ችግሮችንና መንስኤዎቻቸውን በመለየት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚገባ ገልፀው ተመሳሳይ ፈተና የገጠማቸውን አቻ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሞክሮዎችን በመገምገም ግብአት አድርጎ ለመጠቀምና ወደ ትግበራ ለመግባት ከየኮሌጁ የተወጣጣ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸዋል።

የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዲን ዶ/ር ታዬ ገ/ማሪያም ሀገር አቀፍ የድህረምረቃ መግቢያ ፈተና (NGAT) መሰጠት መጀመሩን ተከትሎ የድህረምረቃ መርሃግብርን የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ቁጥር እያሽቆለቆለ መሄዱ ጎልቶ የታየ መሆኑን ገልፀው በዘንድሮው ክረምት ለሚፈተኑ 300 የሚደርሱ ተማሪዎች ፈተናውን ከመውሰዳቸው በፊት አጭር የቅድመ ዝግጅት ስልጠና መስጠት እንደ አንድ መፍትሔ ተደርጎ መተግበሩን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የችግሩ መንስኤዎች ከውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስተው በየደረጃው ሊወሰዱ በሚገባቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ምክክር ተካሂዷል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et