በአፈጻጸም ውል ዝግጅት ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።
የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ዩኒቨርሲቲዎች የመነሻ መረጃ በማሰባሰብና የእርካታ ዳሰሳ ጥናት በማድረግ በሚያዘጋጁትና ውል በሚፈጽሙበት "Performance contracting agreement" ላይ መረጃ ለማሰባሰብና ወደስራ ለመግባት በሚያስችለው ዝግጅት ዙሪያ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስራ ኃላፊዎች ጋር ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም ውይይት አካሂደዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አካ/ጉ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሀ ጌታቸው በውይይቱ ወቅት ባነሱት ሀሳብ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመገምገምና ለመቆጣጠር ያሰበበት የመግባቢያ ሰነድን ለማዘጋጀት ጥራት ያለውና ያልተዛባ መሰረታዊ መረጃን ለማግኘት ዋነኛው መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ቀደም ብሎ መሰረታዊ የመነሻ መረጃ ወይም "Baseline data" የሰበሰበ መሆኑን የጠቆሙት ም/ፕሬዚደንቱ ከአሁን በኋላ ከትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጋር በመሆን መረጃዎቹን የማጥራትና የማሟላት ስራ እንደሚከናወን በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲውና ትምህርት ሚኒስቴር በጋራ በሚገቡት ስምምነት መሰረት ይፈራረማሉ ብለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ሽግግርና ተቋማት ትስስር ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተሾመ ዳንኤል በበኩላቸው የብቃት መመዘኛ ኮንትራቱ በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ አገልግሎት ላይ የተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና የማህበረሰቡን እርካታ ዳሰሳ ጥናት በማካሄድ የሚዘጋጅ እንደመሆኑ ተሳታፊዎች እውነተኛ መረጃን በመስጠትና ቀና ትብብር በማድረግ ተግባራዊነቱን ሊያግዙ እንደሚገባ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት መረጃ ኃይል የሆነበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ የገለጹት አቶ ተሾመ የዩኒቨርሲቲዎችን አቅምና አፈጻጸም ለማሳደግ ብሎም በሚዘጋጁ ዓመታዊና ስትራቴጂክ እቅዶች ላይ በማካተት ለመጠቀም የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታውን የሚገልጽ መረጃ መሰብሰብ እንደሚገባው አሳስበዋል።