በዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ የተመራው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር ቡድን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም በወንዶገነት የደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ጉብኝት አድርገዋል።
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ተሻለ ወ/አማኑኤል ስለኮሌጁ አመሰራረትና ወቅታዊ ቁመና፣ ስለአዲሱ አመት የመማር ማስተማር ጅማሮ፣ ዕድልና ፈተናዎችና ልዩ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በጉብኝቱ የመማሪያ ክፍሎች፣ የተማሪዎች የምግብ ግብዓት ማከማቻና የመመገቢያ አዳራሽ፣ የተማሪዎች ማደሪያ ህንፃዎች፣ የአይ.ሲ.ቲና ዳታ ማዕከል፣ የደህንነት ጥበቃ ማዕከል፣ የአፈር ጥናት ቤተሙከራና ቤተ-መጽሐፍትን ጨምሮ ሌሎች የስራ ክፍሎች የታዩ ሲሆን አሁን ያሉበት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና የአስተዳደሩን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተዋል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለና ምክትል ፕሬዝዳንቶቹ ከጉብኝት መልስ ከኮሌጁ አስተዳደርና መምህራን ጋር በሲዳ አዳራሽ ተወያይተዋል::
ዶ/ር ችሮታው አሁን ላይ እንደሀገር የመንግስት አቅጣጫ ዩኒቨርሲቲዎችን ማስፋፋትና ሙሉ ወጪያቸውን መሸፈን ሳይሆን በትኩረት የተለዩትን ወደ ራስገዝ የመለወጥ እንደሆነ ጠቅሰው ቀደም ሲል በማስፋፋት ስራው ወቅት የተሰሩ አብዛኛዎቹ ህንፃዎች በተለይ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት ላይ የሚታየው መጠነሰፊ ችግር እንደሀገር እንደሚያሳስባቸው ትዝብታቸውን ገልፀዋል:: የህንፃዎቹ እድሳትም ከማስፋፊያ ወጪ በላይ የሆነ አቅም ይጠይቃልና ራሳችንን ለመቻል የምናደርገው ጉዞ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል ካሉ በኃላ ጥራት ላይ በማትኮር ያለንን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ ተመራጭና ተወዳዳሪ መሆን ምርጫ እንዳልሆነ ገልፀዋል:: ከጉብኝቱ ተንስተውም ኮሌጁ በጣም ብዙ እድሎች ያሉት ትልቅ ተቋም መሆኑ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል:: በቀጣይም ወንዶገነት ኮሌጅ እንደስሙ ገነት የሚመስል መሆኑን በበቂ ሁኔታ ማስተዋወቅ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ ማትኮር፣ አለምዓቀፍና የሀገር ውስጥ አጋርነት ላይ የበለጠ መስራት፣ በተመረጡ የትኩረት ዘርፎች ላይ የልህቀት ማዕከል መሆን፣ በተማሪዎች ዘንድ ተመራጭ ለመሆን ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ መመሪያ ሰጥተዋል:: ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳይ የሀገራችንም የዩኒቨርሲቲያችንም ልዩ የትኩረት መስክ እንደመሆናቸው ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር ያስፈልጋልም ብለዋል::