ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር የትብብር ሰነድ ተፈራረመ::
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ሃይቆች ተፋሰስ ውስጥ በፍሎራይድ በተጎዱ አካባቢዎች የፍሎራይድ ቅነሳ ቴክኒኮችንና ቴክኖሎጂዎችን ዲዛይን፣ ሙከራና ማስፋፊያ ፕሮጀክት (FLUORIDE MITIGATION IN THE RIFT VALLEY [FMRV]: PROJECT DESIGN AND PILOTING) በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተፈራርሟል::
በስምምነቱ መሰረት የሁለቱ ተቋማት ትብብር በፍሎራይድ ቅነሳ ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ ምርምርና ስርፀት፣ የአዋጭነት ጥናት፣ በቤተሰብ ደረጃ ጥቅም ላይ የሚውል የፍሎራይድ ቅነሳ ቴክኖሎጂዎች ዲዛይንና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በአጠቃላይ በስምጥ ሸለቆ ሃይቆች ተፋሰስ ውሃ ላይ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የፍሎራይድ መጠን በመቀነስና በህብረተሰቡ ጤና ላይ አደጋ የማያስከትል ንፁህ ውሃ አቅርቦትን በማሻሻል የአካባቢውን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ማሻሻል ላይ ያተኩራል ተብሏል:: የዳሰሳ ጥናቱም በሶስት የተመረጡ የፍሎራይድ ተጠቂ አካባቢዎች ላይ እንደሚሰራ ለማወቅ ተችሏል::
ስምምነቱን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ተፈራርመዋል::