በተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ የተመራው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር መስከረም 28/2017 ዓም በግብርና ኮሌጅ አካላዊ ጉብኝት አካሂዷል::
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ታረቀኝ ዮሴፍ አመራሮቹን ተቀብለው የኮለጁን አሁናዊ ይዞታና የትኩረት መስኮች እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ ገለፃ አድርገዋል:: በጉብኝት መርሃግብሩ ላይ ለውይይት የተጋበዙት የኮሌጁ የስራ ኃላፊዎችም በኮሌጁ አሉ ባሏቸው መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አስተዳደር ሊያግዛቸው የሚገቡ ነጥቦች ላይ ጥቆማ ሰጥተዋል::
ከፍተኛ አመራሮቹ የኮሌጁን ምድረግቢና ህንፃዎች: ቤተሙከራዎች: ቤተ መፃሕፍት: የዶሮ መፈልፈያ ማዕከል: የመሰብሰብያ ቦታዎች: የተማሪዎች አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ጭምር በአካል ጎብኝተዋል::
ከጉብኝቱ ማጠቃለያ ወደ ግብረመልስና ውይይት የተመለሱ ሲሆን ተ/ፕሬዝዳንቱና ሶስቱም ም/ፕሬዝዳንቶች በጋራ የሥራ መመሪያና አቅጣጫ ሰጥተዋል::
ሁሉም ከፍተኛ አመራሮች ግብርና ኮሌጅ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መስራችና አንጋፋ ማዕከል እንደመሆኑ ከምስረታው ጀምሮ ለግማሽ ምዕተ-ዓመት ገደማ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ብቁ ምሁራን ያፈራ ተቋም መሆኑን አስታውሰው ከዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስክ ቀዳሚው የሆነውም ባለው ከፍተኛ እምቅ አቅም ተለክቶ መሆኑን አስምረውበታል::
ፕሬዝዳንቶቹ ኮሌጁ ውስጥ ባዩዋቸው ነገሮች ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን ኮሌጁ መልካም ጅምሮቹንና አፈፃፀሞቹን አጠናክሮ እንዲቀጥል: አሁን ላይ በተለይም በአገልግሎት መስጫ ማዕከላትና የድህረምረቃ ፕሮግራሞች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን እንዲያስተካክል: በውስጥ አቅም መሰራት የሚችሉትን ሥራዎች ግዜ ሳይሰጥ እንዲሰራ: የዩኒቨርሲቲውን ብሎም የመንግስትን እገዛ የሚያስፈልጉት ጉዳዮች ላይ አቅም በፈቀደ መልኩ በልዩ ትኩረት ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ በሚጠበቅበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የአመራሩ ድጋፍ እንደማይለያቸው ተገልፅዋል::