የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የረጅም ግዜ አጋርነት እውቅና ሰጠ::
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀዋሳ ዲስትሪክት ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን ለነበረው የረጅም ግዜ ስኬታማ ትብብር የእውቅና ምስክር ወረቀት የሰጠ ሲሆን በቅርቡ ዩኒቨርሲቲውን ለመምራት በትምህርት ሚኒስቴር ለተመደቡት ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ መልካም የሥራ ዘመን ምኞት መግለጫ አቅርቧል::
የባንኩ ሀዋሳ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ወየሣ ጥላሁን ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ተገኝተው የምስክር ወረቀቱን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለረጅም ግዜ በትብብር እየሰራ መቆየቱን አውስተው በተለይም የኢንተርኔት ባንኪንግ በመጠቀም ፈር ቀዳጅ ተቋም መሆኑን አስረድተዋል:: ባንኩ ለስኬቱ ትልቅ ድርሻ ካላቸው አጋሮች ጋር እንደሚያደርገው ሁሉ በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲው ጋር የቆየውን ትብብር አጠናክሮ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳለው ዳይሬክተሩ አክለዋል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ለተደረገላቸው የመልካም የስራ ዘመን ምኞት መግለጫና ለዩኒቨርሲቲው ለተሰጠው እውቅና አመስግነው ባንኩ ወደፊትም በርካታ የፋይናንሻል ሰርቪስ ሥራዎች ላይ ዩኒቨርሲቲውን እንደሚያግዝ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል:: ፕሬዝዳንቱ በተለይ ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስገዝነት እያደረገ ባለው የሽግግር ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጠንካራ የባንኪንግና ፋይናንስ አጋር አድርጎ ለጋራ ተጠቃሚነት በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል::