የተመራቂ ተማሪዎችን የስራ ፈጠራ ክህሎት ለማሳደግ ስልጠና ተሰጠ::
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኢንተርፕሩነርሺፕ ማዕከልና በደረጃ ዶት ኮም ትብብር የተመራቂ ተማሪዎችን የስራ እድል ፈጠራ እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ ያለመ የሶስት ተከታታይ ቀናት ስልጠና ከህዳር 13-15/2017 ዓም በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተሰጥቷል።
የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ሲናገሩ አንድ ተመራቂ ተማሪ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ሊገበይ የሚገባውና ብቁ ሊያስብሉ የሚችሉት አራት መሰረታዊ ብቃቶች የንድፈ ሀሳብ እውቀት፣ ክህሎት፣ ትክክለኛ አመለካከት እና መልካም ስነ-ምግባር መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህንን ሁሉ ብቃት ለመላበስ የክፍል ውስጥ ትምህርት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ መሰል ስልጠናዎች የተማሪዎችን አጠቃላይ አመለካከት በመቅረጽ ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ስራ ፈጣሪዎች በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ዶ/ር ታፈሰ አክለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የኢንተርፕሩነርሺፕ ማዕከል አስተባባሪ ኢ/ር ትዕግስት አሰፋ እንደገለፁት ከግብርና ኮሌጅ፣ ከዋናው ግቢ፣ ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና ከህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተወጣጡ ስድስት መቶ የሚደርሱ ተማሪዎች በስልጠናው ተሳትፈዋል:: በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን ሆነው የራሳቸውን ስራ በመፍጠር ስኬታማ የሆኑ ባለሙያዎች ተሞክሮዎቻቸውን ለሰልጣኞች እንደሚያካፍሉ የገለጹት ኢ/ር ትዕግስት ይህም የንግድ ፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ተማሪዎች እንደሚያግዝ እንዲሁም ሌሎች ደግሞ የራሳቸውን የስራ ፈጠራ ሀሳብ እንዲያመነጩ እንደሚያነሳሳ ገልጸዋል።
በዕለቱ ልምዳቸውን ካካፈሉ ስራ ፈጣሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሩቋ ወ/ሪት ሐና ሐይሉ በአሁኑ ሰዓት "አብሪ ማይንድ" የተባለ ድርጅት መስርታ የሬዲዮ ፕሮግራም በማዘጋጀትና በተለያዩ የማነቃቂያ መድረኮች ላይ በመገኘት ማህበራዊ አገልግሎት እየሰጠች እንደምትገኝ ገልጻለች። በተጨማሪም የራሷን ድርጅት በማቋቋም ሂደት ውስጥ ስለገጠሟት ፈተናዎችና ስላለፈችባቸው መንገዶች እንዲሁም እንዴት በዙሪያቸው ያለውን እድል በመጠቀም የራስንና የማህበረሰቡን ህይወት ማሻሻል እንደሚቻል ለሰልጣኝ ተማሪዎች ተሞክሮዋን አጋርታለች።
የደረጃ ዶትኮም ክትትልና ቁጥጥር ኦፊሰር የሆኑት ወ/ሪት ውዳሴ አማረ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ በመታገዝ ላለፉት አመታት በስራ እድል ፈጠራ ላይ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም የስራ እድሎችን በማመቻቸት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው አሁን ደግሞ የራሳቸውን የስራ እድል መፍጠር የሚፈልጉ ተማሪዎችን ለማገዝ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንዳለ ተናግረዋል።