ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያስተማራቸውን 67 ወንዶች እና 53 ሴቶች ማለትም 120 ጠቅላላ ሐኪሞችን በዛሬው ዕለት በደማቅ ሥነሥርዓት አስመርቋል::
የሲዳማ ብ/ክ/መ/ጤና ቢሮ ኃላፊና የዕለቱ የክብር እንግዳ ክብርት ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ ለተመራቂ ዶክተሮቹ ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ለሀገር እድገትና ብልጽግና መሰረት መሆኑን ጠቁመው በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት በሚገኘው በጤናው ዘርፍ ላይ የበኩላችሁን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ እንደሆናችሁ አምናለሁ ብለዋል:: የሀ/ዩ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሲዳማና የአጎራባች ክልሎች ኩራት በመሆን በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊነትን እየተወጣ እንደሚገኝ የገለጹት ዶ/ር ሰላማዊት ዩኒቨርሲቲው በየአመቱ የሚያስመርቃቸው ባለሙያዎችም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር የጤና ዘርፉን በብቃት እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል:: ኃላፊዋ በሰጡት የሥራ መመሪያ የዛሬ ተመራቂ ሐኪሞችም በሙያቸው ህዝባቸውን በርኅራኄና በፍፁም አገልጋይነት መንፈስ እንዲያክሙ ለእውቀትም እንዲተጉ አደራ ብለዋል::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በመክፈቻ ንግግራቸው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመማር ማስተማር እንዲሁም በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራ ስኬታማ ከሆኑ የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች አንዱ መሆኑንና በቅርቡ በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶችን ከማስጀመር ባሻገር የተለያዩ የማስፋፊያና የእድሳት ስራዎችን በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። ኮሌጁ በሕክምናና ጤና ሳይንስ ዘርፎች ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ እንዲሁም በህክምና ስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሻሊቲ ጭምር ብቁ ምሩቃንን በማፍራት ለአካባቢውና ለሀገር ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንዳለ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ አሁንም ወደ ራስ ገዝነት በምናደርገው ሽግግር ውስጥ በጥራትና በብቃት ተመራጭ ተቋም እንዲሆን የክልሉን አስተዳደር ጨምሮ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብርና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል::
የኮሌጁ ቺፍ ኤግዘክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ጣሚሶ በበኩላቸው ለተመራቂዎቹ የህክምና ትምህርት በአለምአቀፍ ደረጃ በፈታኝነቱና ከፍተኛ ትጋት በመጠየቁ የሚታወቅ እንደመሆኑ ትምህርቱ የሚጠይቀውን ዋጋ ከፍላችሁ ለቤተሰቦቻችሁና ለሀገራችሁ ኩራት ለመሆን ለዚች ቀን ስለደረሳችሁ በራሳችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል። ዳይሬክተሩ ኮሌጁ በኮምፕሪሔንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታሉ በዓመት ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን የህብረተሰብ ክፍል በሰብ-ስፔሻሊቲ ዘርፎች: የካንሰር ጨረር ህክምና፣ የፎረንሲክ እና ስነምረዛ አገልግሎቶችን ጨምሮ በጨቅላ ህጻናት ህክምና የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ከሁሉም ከፍተኛው ውጤት ያስመዘገበው ዶ/ር በረከት ዘላለም የወርቅ ሜዳልያ እና ከሴቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ዶ/ር ቤተልሔም ደሳለኝ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል::