የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች መላመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሣምንት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ::
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ (ሀዩ-ህጤሳኮ) ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ከጀርሞች መላመድ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክቴር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ከጀርሞች መላመድ ችግር በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚታይ ቢሆንም በሀገሪችን ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ያለ ትክክለኛ የላቦራቶሪ ምርመራና የሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒቶችን በዘፈቀደ መጠቀም ችግሩን ከሚያባብሱ ምክንያቶች ዋነኛው መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር መሳይ ሁኔታውን ለመቀነስ የሚያግዙ ዘመናዊ የህክምና ምርመራ ላቦራቶሪዎች በሁሉም ክልሎች በመቋቋም ላይ እንደሆኑ አስረድተዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው ችግሩን ለማቃለልና የተሻሻሉ መድኃኒቶችን ለማግኘት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የምርምር ዘርፉን ለማጠናከር እየተሰራ ሲሆን የዩኒቨርሲቲውን የላቦራቶሪና የፋርማሲ ባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።
የሀዩ-ህጤሳኮ ቺፊ ኤግዘክዩቲቭ ዳይሬክተር ዓለሙ ጣሚሶ በበኩላቸው በኮሌጁ ስር የሚገኘው ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ከሲዳማ ክልል ባሻገር ለአጎራባች የኦሮሚያና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች መጠነ ሰፊ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በፀረ ተህዋስያን መድሃኒቶች መላመድ ችግር ምክንያት ታካሚዎች ለረዥም ጊዜ ሆስፒታል ውስጥ አልጋ ይዘው ለመቆየት የሚገደዱ በመሆኑ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የፀረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን ያለአግባብ መጠቀም መድኃኒቶች በተህዋስያን በቀላሉ እንዲለመዱና በሽታ ፈዋሽነታቸውን እንዲያጡ ያደርጋል ያሉት ዳይሬክተሩ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በጉዳዩ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለመስራት መታቀዱን ገልፀዋል።
በፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎችና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በሀዩ-ህጤሳኮ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆሰፒታል ስር በአድስ መልክ በዘመናዊ መንገድ እያደረጀ ያለው የምርመራ ላቦራቶሪዎች ጉብኝት አድርገዋል::