በተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ የተመራው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር ቡድን ዛሬ በአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የጉብኝትና ውይይት መርሃግብር አካሂደዋል::

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ወገኔ ማርቆስ አመራሮቹን ሲቀበሉ ስለ ኮሌጁ ታሪካዊ ዳራ: አሁናዊ ቁመናና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ከሌሎች ኮሌጆች ለየት የሚያደርገው ደግሞ ኮሌጁ ሦስት ቦታዎች ላይ ማለትም ሀዋሳ ዋናው ግቢ: አዋዳና አለታወንዶ ላይ የሚሰራ በመሆኑ ለአስተዳደር ትኩረት የማጣት ብሎም ለክትትልና ድጋፍ የማያመች መሆኑን ጠቁመዋል:: እንደ መልካም ዕድል ከተነሱ ነጥቦች መካከል ደግሞ የሚሰጣቸው የትምህርት መስኮች በጣም ተፈላጊ መሆናቸው እና በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ የሚያስተናግድ መሆኑን አንስተዋል::

የከፍተኛ አመራር ቡድኑ በግቢው ውስጥ ያሉ የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በአካል ከጎበኙ በኃላ ከኮሌጁ አመራሮች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ከኮሌጁ አመራሮችና መምህራን ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች ሦስቱም ምክትል ፕሬዝዳንቶች በየዘርፉ ምላሽ ሰጥተዋል::

በመጨረሻም ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በኮሌጁ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ከልብ አመስግነው ኮሌጁ ለዩኒቨርሲቲው የራስገዝነት ጉዞ ትልቅ ድርሻ ከሚወስዱት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የማጠቃለያ ሃሳብና የስራ መመሪያ ሰጥተዋል::

ዶ/ር ችሮታው መንግስት ለዩኒቨርሲቲዎች በየዓመቱ እጅግ ከፍተኛ በጀት መድቦ ቢያስፋፋም ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃን ከማፍራትና ችግር ፈቺ ምርምሮች ሰርቶ ስር ነቀል ሃገራዊ ለውጥ ከማምጣት አንፃር የሚጠበቀውን ውጤት ሊያመጡ ስላልቻሉ በትክክል እንዲያመጡ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በተወሰኑ የትኩረት መስኮች ላይ ጥራትን መሰረት ያደረገ ልየታ ማድረጉን አስታውሰው አሁን ግዜውን የዋጀ አሰራር ለመዘርጋት ያሉትን ሁሉ የትምህርት ፕሮግራሞች ይዘን መቀጠል ስለማንችል በአጭር ግዜ ውስጥ በጥናት ላይ የተመረኮዘ የፕሮግራም ክለሳ ይደረጋል ብለዋል:: እንደተባለው ዩኒቨርሲቲ መምሰል: ራሳችንን ለመቻል ከፍተኛ ጥረት ማድረግና ተወዳዳሪ ሆኖ ፈተናውን ለማለፍ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጥንቃቄ መስራት አለብን ሲሉ ጥሪ አድርገዋል::

ስለራስገዝነት ስናስብ ማወቅ ያለብን መንግስት ማንንም ያለአግባብ ሥራ የማሳጣት ዓላማ ኖሮት ሳይሆን ሁሉም ብቁና ተወዳዳሪ ሆኖ በተቀመጠበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆን ካልቻለ ከውድድር የሚወጣበት አሰራር መዘርጋት ላይ እያተኮረ ነው ያሉት ተ/ፕሬዝዳንቱ አሁን የአስተዳደር ሰራተኛ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ማስተማር ያልቻለ መምህር: ውጤታማ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቦታ አይኖረውምና ሁሉም ኃላፊነቱን አውቆ በየደረጃው በህግ ተጠያቂነት ስሜት ስራውን ካልሰራ ከሲስተም እንዲወጣ እናደርጋለን ብለዋል:: እጁ ንፁህ ሆኖ ሕጋዊ አሰራርን ብቻ ተከትሎ ካልሰራ ማንኛውም ሰው ከተጠያቂነት እንደማይድን አስተዳደሩም ህገወጥነትን እንደማይታገስ ተ/ፕሬዝዳንቱ አስምረውበታል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et