ብሩክ ኢትዮጵያ ለሀዩ የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ሕክምና ፋካሊቲ መምህራንና ቴክኒካል ረዳቶች "ብሩክ ኢትዮጵያ" ከተባለ ግብረሰናይ ተቋም ጋር በመተባበር የክሊኒካል ላብራቶሪ ብቃት ማሻሻል ላይ ያተኮረው ሁለተኛ ዙር ስልጠና ጀምሯል::
የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ዙፋን በደዊ ስልጠናው ሲያስጀምሩ "ብሩክ ኢትዮጲያ" በስልጠና ዝግጅት፣ በቁሳቁስ አቅርቦት እንዲሁም የግንባታ ድጋፍ በማድረግ በተለያዩ ወቅቶች ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በዚህም የተነሳ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና ማስፋት መቻሉን ተናግረዋል። ዲኗ ስልጠናው የእንስሳትን ደህንነትና ጤንነት ከማረጋገጥ አኳያ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
የእንስሳት ህክምና ፋካሊቲ ዲን ዶ/ር አመነ ፍቃዱ በበኩላቸው ድርጅቱ በመጀመሪያው ዙር ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለተወጣጡ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠቱን ጠቁመው ይህኛው ዙር ስልጠና አላማውን ከእንስሳት ደህንነትና አያያዝ ጋር ተያይዞ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ታስቦ እንደ ተዘጋጀ ገልጸዋል። በዚህም ተማሪዎችና ተመራማሪዎች የእንስሳት ህክምና ምርምሮቻቸውን ለማሳደግ በቀጥታ በእንስሳቱ ላይ ከመሞከራቸው በፊት በላብራቶሪ በተዘጋጁ የእንስሳት ሞዴሎች ላይ በመሞከር ብቁ እንዲሆኑ የሚያስችል ክህሎት ይላበሳሉ ብለዋል።
በብሩክ ኢትዮጵያ የስራ ቁጥጥርና ግምገማ ኃላፊ ዶ/ር ቸርነት አበራ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የእንስሳት ደህንነትን ማስጠበቅ ላይ የሚሰራ ተቋም እንደመሆኑ የመምህራንንና የተመራቂ ተማሪዎችን እውቀት ለማሳደግ ከአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ዶ/ር ቸርነት ጨምረውም በዛሬው ዕለት ቀደም ተብሎ የተሰጠውን ስልጠና ያጠናቀቁ መምህራን ሰርተፊኬት እንደተበረከተላቸው ገልጸው ሁለተኛው ዙር ስልጠና ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።