ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት መስከረም 24/2017 ዓ.ም ተፈራርሟል።
የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሺፈራው ሰለሞን በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የ41 ዓመታት እድሜ ያለው አንጋፋ ተቋማቸው ከአንጋፋው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር ብዙ የትብብር ዘርፎች ላይ ውጤታማ ሥራ መስራት እንደሚፈልግ ገልፀዋል:: ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደልማት ተቋማት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ብዙ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች እንጠብቃለን ብለዋል።
የኢንጂነሪንግ ማማከር ዘርፍ ማናጀር የሆኑት ዶ/ር ዘካርያስ ገብረየስ ስለ ተቋማቸው ባቀረቡት አጭር ማብራሪያ ላይ በሲዳማ ክልልና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ሳተላይት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማስፋፋት ዕቅድ ስላለ በበርካታ ዘርፎች ላይ በትብብር የመስራት ዕድል አለ ብለዋል። ተቋሙ በዋናነት በኢንቨስትመንት: የሰው ሀብት አስተዳደር: አካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች: የገበያና የኦፕሬሽናል በመሳሰሉት ዘርፎች የማማከር: የማሰልጠን እና በአስተዳደር ዘርፎች ላይ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ እንደሆነ ዶ/ር ዘካርያስ አብራርተዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ም/ቴ/ሽ/ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በበኩላቸው ኢንዱስትሪው ከዩኒቨርሲቲ ጋር በሙያዊ የማማከርና ስልጠናዎች በመስጠት: የሰራተኞች ልውውጥና የተማሪዎች ተግባር ተኮር ስልጠና እንዲያገኙ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በጋራ ለመስራት ስምምነቱ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። አክለውም ሁሉም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከጠቅላላ በጀታቸው ላይ 0.1% የሚሆነውን ለምርምር እንዲመድቡ የወጣው አዲሱ የመንግስት አቅጣጫ ለሁለቱም ተቋማት በትብብር ለመስራት መልካም ዕድል ስለሚፈጥር ትብብሩ ለሁላችንም ይጠቅማል ሲሉ የሁለትዮሽ ስምምነቱን ጠቀሜታ አጉልተዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ እንደዚሁ የተቋሙን አመራሮች ወደ ዩኒቨርሲቲው ለትብብር መምጣታቸውን አመስግነው የዚህ ዓይነቱ የመንግስትን አላማም የሚደግፍ እንደመሆኑ ስምምነቱ ከውል ፊርማ ባለፈ መሬት ላይ ወርዶ ወደሥራ ለመግባት ተናብበን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።