ለሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መካከለኛ ደረጃ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የም/ቴ/ሽ/ም/ፕ/ጽ/ቤት ስር የሚገኘው የኢንተርፕሩነርሺፕና ቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ዳይሬክቶሬት ከኢትዮጲያ ኢንተርፕሩነርሽፕ ኢንሲቲትዩት ጋር በመተባበር ”ፐብሊክ ኢንተሩፕነርሽፕና ኢኖቬሽን ኢኮሲስተም ግንባታ“ በሚል ርዕስ ዙሪያ ከተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተዉጣጡ መካከለኛ ደርጃ አመራሮች ተግባር-ተኮር የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ ነው።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታዉ አየለ በመክፈቻ ንግግራቸው የሀገርም ሆነ የተቋም ግንባታ በዘለቄታዊነት እዉን የሚሆነዉ የተሻለና ብቁ አመራር ሲፈጠር መሆኑን አዉስተዉ ዩኒቨርሲቲዉ ያለበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት በየዘርፉ ብቃት ያላቸዉን አመራሮች መመደብና ተፈጻሚ የሚሆን ህግና ስርአት መዘርጋት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል:: ይሄንንም ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል መሰል የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በቀጣይም በሁሉም ደረጃ ለሚገኙ አመራሮች እንደሚሰጥ ተ/ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ በበኩላችው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ ከሚገኙ መሰል ተቋማት አንፃር የተሻለ ሀብት እንዳለዉ ጠቅሰዉ በተለያዩ ምክንያቶች ያለውን ሀብት አሟጥጦ የመጠቀም ችግር እንደሚሰተዋልና ይህን ችግር ለመፍታት የተሻለ አመራር መፍጠር በዚያም በእጅ ያለን ሁሉን አቀፍ ሀብት አሟጦ በተገቢዉ መንገድ መጠቀም የዩኒቨርሲቲዉ ህልዉና በመሆኑ ሁሉም አካላት የሚጠበቅባቸዉን መወጣት እንዳለባቸዉ አሳስበዋል። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ብቁ አመራር መፍጠር የግዲታ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ታፈሰ የዛሬዉ የአቅም ግንባታ ስልጠናም ይህን ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ከተለያዩ ኮሌጆችና የአስተዳደር ክፍሎች የተዉጣጡ ከሀምሳ በላይ የመካከለኛ ደረጃ አመራሮች ተካፋይ ሆነዋል።