የትምህርት ዘመኑ ማስጀመሪያ ጠቅላላ የመምህራን ጉባኤ ተካሄደ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ2017 ዓም የትምህርት ዘመን መጀመርን አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ከሁሉም ኮሌጆች መምህራን ጋር ስለ አዲሱ የትምህርት ዘመን ዋነኛ የትኩረት አጀንዳዎች በዋናው ግቢ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ውይይት አካሂደዋል::

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ስመጥር ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የመሆን ራዕይ ይዞ እየሰራ ያለው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ይህንን እቅድ ከግብ ለማድረስ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ዶ/ር ችሮታው አክለውም  ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዩኒቨርሲቲ ቁመና ላይ ለመገኘት እንዲችል መምህራን የተሻለ አስተዋፅኦ ለማበርከት ራሳቸውን ማብቃት እንደሚጠበቅባቸውና ዘመኑን የዋጁ የመማር ማስተማር ስርአቶችን መላመድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውይይቱ መነሻ ላይ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሀ ጌታቸው፣ የም/ቴ/ሽ/ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ታፈሰ ማቲዎስ እንዲሁም የአስተዳደርና ልማት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ በየዘርፋቸውን ያሉትን ቁልፍ የትኩረት አጀንዳዎች ለይተው ለተሳታፊዎች ገለፃ አድርገዋል::

ምክትል ፕሬዝዳንቶቹ በመድረኩ ካተኮሩባቸው ቁልፍ አጀንዳዎች መካከል ጥራትና አግባብነት ያለውን ትምህርት ለመስጠት ዲጂታላይዜሽንን መጠቀም እንደሚገባ፣ ራስ-ገዝነት በተቋማዊ፣ የሰው ሀብት፣ የአካዳሚክና የኢኮኖሚ ነጻነት የሚገለጽ እንደመሆኑ በሁሉም ዘርፍ የጠራ የትኩረት አቅጣጫ በመለየት ተፈጻሚነቱን ማፋጠን እንደሚገባና ምርምርና የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስርን ማጠናከር ለዚህ አስፈላጊ መሆኑን፣ ብሎም በአስተዳደር ዘርፍ ከሰው ኃይል አንጻር ብቃት ላይ የተመሰረተና አግባብነት ያለው የሰራተኞች ድልድል ማድረግና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠትና በዩኒቨርሲቲው የተጀመሩ አዳዲስና ጥገና የሚሹ የሕንፃ ግንባታዎችን ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ ለማጠናቀቅ ሊሰራ እንደሚገባ የሚሉት ይጠቀሳሉ።

በጠቅላላ ጉባኤው ከተሳተፉ መምህራን በርካታ ጥያቄዎችና የአሰራር ማሻሻያ ሃሳቦች ለአመራሩ የተሰነዘሩ ሲሆን ዋና ትኩረት የሚሹ ሃሳቦች የመምህራን የኑሮ ውድነት ተግዳሮቶችን በተለይም የመኖሪያ ቤት ችግር የሚቀረፍባቸው መንገዶች፣ የትምህርት ጥራትንና ራስገዝ ለመሆን የሚደረገው ጉዞ የትምህርት ግብአቶች አቅርቦትና ጥራትን ጨምሮ መሻሻል የሚገባቸው መልካም የሥራ ከባቢ የመፍጠር እርምጃዎች፣ የሀብት ብክነትን የመቀነስና የምርምር ውጤቶች ህትመት የሚደገፍበት ዘዴ፣ ከኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት አንፃር መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው::

ተ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው በጉባኤው ማጠቃለያ ሃሳባቸው ተቋሙ አቅዶ የተነሳቸውን ራዕይና ተልዕኮ ለማሳካት መምህራንና ተማሪዎችን እንዲሁም የአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞችን በግልፀኝነትና ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ካላስተዳደረ እቅዱ ብቻውን መሬት ላይ መውረድ እንደማይችል ጠቁመው ሁሉም በቅንነት ከአመራሩ ጎን በመሆን ለጋራ ስኬት ሊተጋ እንደሚገባ አሳስበዋል:: በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ሊደርስበት ካለው የትልቅነት ራዕይ ለማድረስ አመራሩ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ላይ እንደሚያተኩር፣ መሰረታዊ የመማር ማስተማር እንዲሁም የምርምር ሥራዎችን የሚደግፉ ግብዓቶችና መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ፣ የሃብት ብክነትን በማስወገድና ወጪን በመቀነስ እንዲሁም ቀደም ሲል የተዘረጉ መሰረተ ልማቶችን እያደሱ በእንክብካቤ መያዝ እንደሚገባ፣ እንደሀገር ፈታኝ የሆኑ የኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ የመምህራን ችግሮች በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሊቃለሉ የሚችሉባቸው አማራጮች ላይ በጋራ እንደሚሰራ ገልፀዋል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et