"ኢትዮ-ሀዩ ቅድመ-ጽንሰት ጤና እና ጤና ክብካቤ ኢኒሼቲቭ" ላይ አውደ ጥናት ተዘጋጀ

የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት አንዱ በሆነው "ኢትዮ-ሀዩ ቅድመ-ጽንሰት ጤና እና ጤና ክብካቤ ኢኒሼቲቭ" ላይ የመግባብያ እና የጋራ ግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናት ተዘጋጀ።

ሚያዚያ 28/2014ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ዋናው ግቢ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ ዝግጅት ላይ ከፌደራል፣ ከሲዳማ እና የደ/ብ/ብ/ህ ክልል የመጡ የበላይ አመራሮች፣ የተመረጡ ባለሙያዎች፣ የማህበረሰብ ተወካዮች እና አጋር የሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነውበታል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት  የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጽ/ቤት ም/ፕሬዚደንቱ ዶ/ር ታፈሰ ማቴዎስ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የምርምር ዩኒቨርስቲ እንደመሆኑ በርካታ ምርምሮችን በጤናው ዘርፍ በየወቅቱ ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸው፤ በዛሬው እለትም በዶ/ር አንዳርጋቸው ካሳ እና ባልደረቦቹ ሲከናወን የነበረው በቅድመ-ጽንሰት ህክምና ላይ ያተኮረው የምርምር ስራ ተጠናቆ ለውይይት መቅረቡን ተናግረዋል። አክለውም የዛሬው ዝግጅት በጤናው ዘርፍ ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰነውን ይህን የምርምር ስራ ወደ ተግባር ለማውረድ በሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች፣ የአሰራር ስርዓቶች እና ተግዳሮቶች ላይ ውይይት በማድረግ፤ የድርጊት መርሀ-ግብር ላይ የመፍትሄ ሀሳቦችን ማቅረብ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑትና በቅድመ-ጽንሰት ህክምና ምርምር ላይ ዋና ተመራማሪ የነበሩት ዶ/ር አንዳርጋቸው ካሳ በበኩላቸው እንደ ሀገር ሲታይ በቅድመ ጽንሰት ህክምና ላይ ያለው እውቀት እና በመንግስትም የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ገልጸዋል። ይህንንም ክፍተት ለማሻሻል በማሰብ እርሳቸው እና ባልደረቦቻቸው በጋራ በመሆን ላለፉት ጊዜያት ምርምር ሲያካሂዱ መቆየታቸውን፤ በዚህም መሰረት ያገኙት ውጤት ለፌደራል ጤና ሚኒስትር ቀርቦ በሀገሪቱ የጤና ስርዓት ውስጥ ተካቶ ተግባራዊ እንዲሆን መመሪያ መተላለፉን ተናግረዋል። ዶ/ሩ ቀጥለውም ይህ አውደ ጥናት በኢትዮጵያ በተቀዳሚነትም በሲዳማ እና የደ/ብ/ብ/ህ ክልሎች የጤና ስርዓቶች ውስጥ የቅድመ ጽንስ ጤና እና የጤና ክብካቤን በማስረጽና በመተግበር ረገድ የሚደረጉትን ስራዎች ለማገዝ ያለመ ነው።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት የእናቶች ጤና ቡድን አስተባባሪ የሆኑት ሲ/ር ዘምዘም መሐመድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው የሀገሪቱን የጤና ደረጃ ለማሻሻል የጤና ባለሙያዎችን በማብቃት፣ የጤና ተቋማትን በማዘመን እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል። ይህንን ተግባር ለማገዝም በዛሬው እለት በቅድመ-ጽንስ ህክምና ላይ የተካሄደው የምርምር ስራ ከዚህ ቀደም በቅድመ ወሊድ ላይ ሲተገበር የነበረውን ስራ ወደ ተሻለ ደረጃ በማሳደግ፤ ካልታሰበ እርግዝና ጋር ተያይዞ በእናቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጠረውን ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንሰው ገልጸዋል። ይህ በሲዳማ እና የደ/ብ/ብ/ህ ክልል ተግባራዊ የሚደረገው በፓይለትነት ለሀገር አቀፍ ስራዎች ግብዓት የሚሆኑ ጠቃሚና አጋዥ ተሞክሮዎች ሊገኙበት እንደሚችል ታምኖበታል ብለዋል።

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et