በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐግብር ተካሄደ::
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በየዓመቱ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ምክንያት በማድረግ የዘንድሮውን የችግኝ ተከላ መርሐግብር ዛሬ ጠዋት በዋናው ግቢ ከ2 ሺህ በላይ የተለያዩ ችግኞችን የመትከል ፕሮግራም አካሂዷል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ዩኒቨርሲቲው በወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም በግብርና ኮሌጆች በሚገኙ የእጽዋት ማበልጸጊያ ማዕከሎቹ ለምግብነት፣ ለአፈርና አየር ጥበቃ የሚውሉ ሀገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞችን በማፍላት ለሀገር አቀፍ ንቅናቄው የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ መቆየቱን ገልጸዋል። በዛሬው ዕለትም በዋናው ግቢ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ክፍሎች የአረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያሳረፉ ጠይቀው ከሰሞኑ ያስተዋልናቸውን ዓይነት አሰቃቂ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል ብሎም የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ይረዳን ዘንድ ችግኞችን መትከል እንዲሁም መንከባከብ የሁሉም ሰው ግዴታ መሆኑን አሳስበዋል::
የማህበረሰብ ጉድኝትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ፍሰሀ በበኩላቸው ሀገራችን የአየር ንብረት ለውጥንና ተጽዕኖዎቹን መቋቋም እንድትችል መንግስት የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርን ቀርጾ ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውሰው ዩኒቨርሲቲው ይህንኑ በማስመልከት በማህበረሰብ አገልግሎት በኩል በተለያዩ ወረዳዎች የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት እንዲሁም የተጎዱ መሬቶችን በማከም ውጤታማ ስራ መስራቱን ተናግረዋል። አቶ ማርቆስ አክለውም በመርሐግብሩ ከ2,000 በላይ የሚሆኑ ምርጥ የቡና ዝርያዎች እንዲሁም ከ5,000 በላይ ሌሎች ችግኞች በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንደሚተከሉ ገልጸው በቅርቡ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን የመሬት መንሸራተት አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል መሰል የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ሊስፋፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የውጭ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እመቤት በቀለ በመርሐግብሩ ላይ ተገኝተው ሀሳባቸውን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ተፈጥሮን መንከባከብ የሰው ልጆች ሁሉ ኃላፊነት እንደመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለመሰል ሀገርአቀፍ አጀንዳዎች የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ሀገራዊ አጀንዳውን በማሳካት አረንጓዴና ለአየር ንብረት ለውጥ በቀላሉ የማትበገር ሀገር መገንባት፣ ገቢ ማስገኘትና የአካባቢ ጥበቃን ማሳደግ ችግኞችን መትከል ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል ዋነኞቹ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር እመቤት ዩኒቨርሲቲው በምርምር የበለፀጉና የተሻሻሉ ችግኞችን ለአካባቢው ማህበረሰብ በማሰራጨት የራሱን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል::