የትምህርት ኮሌጅ ለሶስተኛ ድግሪ የኮሌጁ ተማሪዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ኮሌጅ በኮሌጁ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ለሚማሩ የሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎች በአካዳሚክ አፃፃፍ ክህሎት እና የምርምር ውጤቶችን በታዋቂ ጆርናሎች ለማሳተም በሚረዳ አፃፃፍ ዘዴ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና ከመጋቢት15-16/2014 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡
ዶ/ር አብርሃም ቱሉ የትምህርት ኮሌጅ ዲን እንደተናገሩት ይህ ስልጠና በኮሌጃችን በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ለሚማሩ የሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎች በአካዳሚክ እና በምርምር ህትመት አፃፃፍ ላይ ያሉባቸውን ክፍተቶችን ለመሙላትና ወደፊትም ውጤታማ ሆነው እንዲገኙ ለማስቻል የታሰበ የአቅም ግንባታ ስልጠና ነው፡፡
ዲኑ አክለውም ስልጠናውን እንዲሰጡልን የጋበዝናቸው ፕ/ር በለጠ ከበደ በአሜሪካን ሃገር ኒውዮርክ በሚገኘው ሜዲሊ የትምህርት ት/ቤት እንዲሁም በቴክሳስ ቤኪ ግራጂት ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ድግሪ ተማሪዎችን የሚያስተምሩ፣ የሚያማክሩና በዘርፉም በርካታ ምርምሮችን ያበረከቱ ሲሆን በስርዓተ- በትምህርት ክለሳ፣ በአፀደ ህፃናት ትምህርት፣ በትምህርት ጥራትና ዕውቅ አሰጣጥ ዙሪያ በርካታ ምርምሮች ያደረጉ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ፕሮጀክት ላይ መሪ ተመራማሪ እና አለማቀፍ አማካሪ መሆናቸውን ገልፀው እዚህ ድረስ ጥሪያችንን ተቀብለው ሊያሰለጥኑልን በመምጣታቸው በኮሌጁ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
ሰልጣኞችም በሁለት ቀን ስልጠና በርካታ ክህሎቶችን፣ የልምድ ልውውጥና ተሞክሮ ዓለም አቀፍ ተመራማሪና ምሁር ከሆኑት ፕ/ር በለጠ ከበደ ማግኘታቸውን እና ከስልጠናው ያገኙትንም ክህሎት ወደፊት በሚሰሯቸው የምርምር ፅሁፎች ላይ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡