የትምህርት ኮሌጅ ለመጀመሪያ ድግሪ 2ኛ ዓመት ተማሪዎች አቀባበልና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አዘጋጀ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ትምህርታቸውን ተከታትለው እንደየምርጫቸውና ውጤታቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ ተማሪዎች በየኮሌጁ እንደተመደቡ የሚታወቅ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው የሚገኘው የትምህርት ኮሌጅም ወደ ኮሌጁ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ለመማር ለመጡ የመጀመሪያ ድግሪ 2ኛ ዓመት ተማሪዎች በመጋቢት 15/2014ዓ.ም የእንኳን ደህና መጣችሁና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡
የትምህርት ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር አብርሃም ቱሉ ወደኮሌጃችን መርጣችሁን ስለመጣችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ እያልኩኝ በዛሬው መርሐ-ግብር ለኮሌጁ አዲስ ተማሪዎች እንደመሆናችሁ በኮሌጁ ስለሚገኙት የትምህርት ክፍሎችና ስለ ዩኒቨርሲቲው ህግና ደንቦች ገለፃ የሚደረግላችሁ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ቆይታችሁም እንዴት ውጤታማ ተማሪዎች መሆን እንደምትችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እና ከኮሌጁ ውጤታማ ተማሪዎችም የልምድ ልውውጥ እንድታደርጉ ታስቦ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር አብርሃም አክለውም ተማሪዎቻችንም በዚህ አፍላ ዕድሜያችሁ ብዙ ፍላጎት ቢኖራችሁም ለሁሉም ነገር ግን ጊዜና ወቅት መኖሩን በመረዳት ቅድሚያ ለሚገባው ዓላማችሁ ትኩረት በመስጠት፣ ትምህርታችሁን አጥብቃችሁ በማያዝ እና ጥሩ ውጤት በማምጣት ለእህትና ለወንድሞቻችሁ አርዓያ እንድትሆኑ እያሳሰብኩ ወደፊት ብቁና ተወዳዳሪ የትምህርት ባለሙያ በመሆን እንድታገለግሏት ሀገራችሁ ከእናንተ ብዙ ትጠብቃለችና አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅና ፈጠራ ላይ በማተኮር በእውቀት የተገነባ፣ በክህሎትና በስነምግባር የታነፀ ባለሙያ ሆናችሁ እንድትወጡ አደራ እያልኩኝ በኮሌጁ በኩልም ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን እናንተን ለመደገፍና ክትትል ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉንና ቁርጠኛ መሆኑን ላሳውቃችሁ እወዳለሁኝ ብለዋል፡፡
ተማሪዎችም በተደረገላቸው አቀባበልና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ደስተኛ መሆናቸውን በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ ካገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡