የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተጠናቀቁ የምርምር ስራዎችና የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች ላይ ግምገማ አካሄደ።
መጋቢት 15/2014 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሲካ ቤቴ እንደገለጹት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ከሚገኙ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንደመሆኑ በየወቅቱ የሚካሄዱ ምርምሮችን ሲገመግም እና ወደ ተግባር ሲያስገባ ቆይቷል። በማስከተልም ይህ ግምገማ በተጠናቀቁ ስምንት የምርምር ስራዎች ላይ ያተኮረ መሆኑን እና በእነዚህ የምርምር ሂደቶች ላይ የተገኙ ውጤቶች፣ ያሉ ተግዳሮቶች እና ልንማርባቸው የሚገቡ ስራዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ብለዋል። አክለውም በተያዘው 2014 ዓ.ም በሂደት ላይ ያሉ ሁለት የቴማቲክ እና ስምንት የዲሲፕሊነሪ የምርምር ፕሮጀክቶች እንደሚገኙ እና ከዚህም ውስጥ 3ቱ በሴቶች ላይ ያተኮሩ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ባዩ በበኩላቸው ቀደም ሲል ተጀምረው የተጠናቀቁ ምርምሮች ቀርበው በመምህራን እየተገመገሙ እንደሚገኙ ተናግረው በምሳሌነት ከጠቀሷቸው የምርምር ስራዎች መካከል ቡና አብቃይ በሆነው የሲዳማ ክልል ላይ ቡናን በማጠብ ሂደት ውስጥ የሚወገዱ ውጋጆች በማህበረሰቡና በአካባቢው ላይ ጉዳት በማያደርሱበት ሁኔታ እንዲወገዱ ማድረግ፣ በወንዶ ገነት በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ የማድረግ ስራ መስራት እና በአራት ቋንቋዎች ማለትም አማርኛ፣ ትግረኛ፣ ሲዳምኛ እና ወላይትኛ ቋንቋዎችን በኮምፒውተር ለመጠቀም እንዲቻል ዘንድ የቋንቋ ክምችት መደረጉን እንደማሳያ አንስተዋል።
በዕለቱ ከምርምር ገምጋሚዎች መካከል አንዱ የሆኑት እና ከኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ እና ማኔጅመንት ክፍል የመጡት ዶ/ር ደሳለኝ ግርማ ሲናገሩ በመንግስት በጀት የሚደገፉት ምርምሮቻችን ምን ደረጃ እንደደረሱ እና ምን አይነት ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንደነበሯቸው ለማየት መሰል ግምገማዎች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። አክለውም እንደ ዩኒቨርሲቲ ብሎም እንደ ሀገር የምርምር ዘርፉ እያደገ እንደሚገኝ እና በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሀርቪክስ እና ወተር ሶርስ ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ጎንሴ አመሎ በእለቱ አንድ የምርምር ስራ ያቀረቡ መሆኑን ገልጸው በዕለቱ ከተሰጣቸው አስተያየቶችም ብዙ እንደተማሩ በማንሳት መሰል ግምገማዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም ተመራማሪዎች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈው የምርምር ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ እንደመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢው እገዛ እና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።