አስራ ስድስተኛው የቲቢ የምርምር ጉባኤ መካሄድ ጀመረ

አስራ ስድስተኛው የቲቢ የምርምር ጉባኤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መካሄድ ጀመረ፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከጤና ሚኒስቴር እና ከሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ቲቢን ለማጥፋት የድርሻችንን እናበርክት ፤ ሕይወትን እንታደግ በሚል መሪ ቃል አመታዊ ብሔራዊ የቲቢ የምርምር ጉባኤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከመጋቢት 13-15 ቀን 2014 ዓ.ም እያካሄደ ይገኛል፡፡

ዶ/ር አያኖ በራሶ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እንደገለፁት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ እና በርካታ ተመራማሪዎች ያሉበት ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ የዚህ መሰሉን ብሄራዊ የቲቢ የምርምር ጉባኤን ማዘጋጀቱ የቲቢ በሽታን በሚመለከት በርካታ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዓለም አቀፍናአጋር ድርጅቶች እንዲሁም ተሳታፊዎች በመገናኘት እውቀታቸውን እና ልምዳቸውን እንዲለዋወጡ፣  በችግሩና መፍትሄውም ላይ ለመምከር መልካም አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡

ዶ/ር አየለ ተሾመ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በጉባኤው መክፈቻ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ ስርጭት ለመግታት እና ለማጥፋት ዘመናዊ የምርመራ መሳሪያዎችን በጤና ተቋማት በማስገባት አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ እና በየአምስት ዓመቱ የሚተገበር ዕቅድ በማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው አመታዊ ብሔራዊ የቲቢ የምርምር ጉባኤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መደረጉ ፋይዳው የጎላ ከመሆኑም ባሻገር አገራችን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት እና የተለያዩ ግጭቶች ምክንያት በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት፣ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ መስተጓጎል፣ የህዝብ መፈናቀል፣ የድርቅ መስፋፋትና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያቶች በቲቪ በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች እንዳይቀለበሱ በትጋትና በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው በአስራ ስድስተኛው የቲቪ የምርምር ጉባኤ ላይ ከ2022 እስከ 2026 እ.ኤ.አ ተግባራዊ የሚደረግ ሶስትኛ ዕትም ብሔራዊ የቲቢ ምርምር ፍኖተ ካርታን ይፋ አድርገዋል፡፡

አቶ ታየ ለታ የጤና ሚኒስቴር የቲቢ በሽታ ኬዝ ቲም አስተባባሪ ኢትዮጵያ የቲቪ በሽታ ከተሰራጨባቸው ሰላሳ ሃገራት አንዷ እንደነበረች እና አሁን በተሰራው ከፍተኛ ስራ ከዝርዝሩ መውጣቷን አውስተው መድኃኒት የተላመደ ቲቢን አክሞ በማዳንም ውጤታማ ከተባሉ አምስት ሃገራት አንዷ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

ለሶስት ቀናት እየተካሄደ ባለው በዚህ ጉባኤ ከአለም ጤና ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና አጋር ድርጅቶች የተገኙ ተመራማሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን በርካታ የምርምር ስራዎችም ቀርበው ውይይትና ምክክር ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

 

 

 

 

 

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et