የፖሊሲ ልማትና ጥናት ተቋም በሴት ስራ ፈጣሪዎች ላይ ያተኮረ የምርምር ፕሮጀክት ጀመረ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ልማትና ጥናት ተቋም ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ በሴት ስራ ፈጣሪዎች የቢዝነስና ህይወት ተሞክሮ ላይ የሚያተኩር የፖሊሲ ምርምር ፕሮጀክት ጀምሯል፡፡ ሴት ስራ ፈጣሪዎች በስራቸውና በኑሮ ተሞክሯቸው የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመለየት ቢዝነሳቸውን በተሻለ ሁኔታ ፋይናንስ ማድረግ የሚችሉባቸውን የ ፖሊሲና የአሰራር አማራጮች ማመላከት የጥናቱ ትኩረት ነው፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ልማትና ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ፕ/ር ተስፋዬ ሰመላ በመክፈቻው ላይ ተገኝተው ተቋሙ ከዚህ ቀደም ለሀገራችን ፖሊሲ አውጭዎች ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ምርምሮችና ጥናቶችን ለተለያዩ አጋር አካላት በማድረግ የራሱን ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ እንዳለ ገልፀው በዚህ ፕሮጀክትም ወጣት ተመራማሪዎቻችን አቅማቸውን በማጎልበት ችግር ፈቺ ምርምርና ጥናቶችን እንዲያደርጉ መልካም ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም ተመራማሪዎቹ ዕድሉን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበው ፕሮጀክት ፅፈው በማምጣት ይሄንን እድል ላመቻቹት የተቋሙ ተመራማሪና የፒኤችዲ ፕሮግራሞች አስተባበሪ ዶ/ር መልሰው ደጀኔ፣ ጥናቱን በገንዘብ ፋይናንስ ያደረገውን የአለም ባንክን፣ ስልጠናውን በመስጠት ላይ ላሉትና በአለም ባንክ በኩልም ፕሮጀክቱን በመምራት ላይ ለሚገኙት ተመራማሪዎችና የስራ ኃላፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ከአለም ባንክ በኩል ጥናቱን ዶ/ር ሬቼል ፒየሮት እና ዶ/ር ሶፊያ ፍሬድሰን -ሬይደኖር ይመሩታል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በስልጠናው የሚሳተፉ ወጣት ተመራማሪዎችን በመረጃ ስብሰባና ተያያዥ ጉዳዮች ለአምስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና በምርምር ቡድኑ ባልደረባ በ ሚስተር ፓራጃት ቻክራባርቲና በፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር መልሰው ደጀኔ ከየካቲት 22/2014ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ሲሆን ዶ/ር ፍሬድሰን - ሬይደኖር እንዲሁም የፕሮጀክቱ ሌላዋ ባልደረባ ሎረን ማሪኖ በበየነ መረብ አማካኝነት ገላፃ ያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡