ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር ተዘጋጀ

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር ተዘጋጀ።

በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኢንስቲትዩትና የሁሉም ኮሌጅ ዲኖች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነውበታል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ዩኒቨርሲቲው በየአመቱ ለሚቀላቀሉት አዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም በማዘጋጀት ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በቀላሉ እንዲቀላቀሉ እያደረገ መቆየቱን ጠቅሰው በዚህ አመት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን መርጠው በመምጣታቸው ዩኒቨርሲቲው ደስ መሰኘቱን ለተማሪዎች ገልጸዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም ዩኒቨርሲቲው በውስጡ በያዛቸው ሰባት ካምፓሶች በበርካታ የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን ተቀብሎ በቂ እውቀትና ክህሎት አንግበው እንዲወጡ እየሰራ እንደሚገኝና አዲስ ገቢ ተማሪዎችም በግቢው በሚኖራችው ቆይታ የመጡበትን አላማ ለማሳካት በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል። ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያዊ ማንነት መገለጫ በመሆኑ ከቀለም ትምህርት ባሻገር ተማሪዎች የእርስበእርስ ተግባቦትና አብሮ የመኖር እንዲሁም አብሮ የመስራት ባህልን ለማሳደግ ሊሰሩ እንደሚገባ ዶ/ር አያኖ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ዳይሬክተር ወ/ሮ ምህረት ገነነ በበኩላቸው ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ከሚረዷቸው ነገሮች መካከል ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም አሉታዊ ከሆነ የአቻ ግፊት እራሳቸውን መጠበቅ ዋነኞቹ መሆኑን ገልጸዋል። ዳይሬክተሯ ጨምረውም ለተማሪዎቹ የህይወት ክህሎት ስልጠናና የምክር አግልግሎት የሚያገኙበት መንገድ የተመቻቸ በመሆኑ ይህንኑ በአግባቡ በመጠቀም ለራሳቸውና ለሀገራቸው የተሻለ ነገን ለመፍጠር ሊሰሩ እንደሚገባ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለተማሪዎቹ የሕይወት ክህሎት ስልጠና የተሰጠ ሲሆን በመጨረሻም ከሁሉም ኮሌጆች እና ኢንስቲትዩቶች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት በመስጠት የዕለቱ ፕሮግራም ፍጻሜውን አግኝቷል::

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et