የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማ/ብ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከተማሪ ወላጆች ጋር ውይይት አካሄደ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ውይይት ላይ የትምህርት ኮሌጅ ኃላፊዎች: መምህራን እና የተማሪ ወላጆች ተገኝተውበታል።
የትምህርት ኮሌጁ ዲን ዶ/ር ሳሙኤል አሰፋ በያዝነው አመት ወደ ስራ የሚገባውን ሞዴል ት/ቤት ለማቋቋም ረዘም ላለ ግዜ ጥናት ሲካሄድ መቆየቱንና ቀደም ሲል ስራውን ከጀመሩ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የልምድ መቅሰም ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። ዲኑ ሞዴል ት/ቤቱ የመማር ማስተማር ስራውን ከመጀመሩ በፊት ከመምህራን እና ከተማሪዎች ጋር ጥልቀት ያለው ውይይት ማካሄዱን አስታውሰው አሁን ደግሞ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር በማሰብ ከተማሪ ወላጆች ጋር የውይይት መድረክ ማዘጋጀት ማስፈለጉንና በዚህ ውይይትም ከወላጆች አስፈላጊውን ግብአት በመቀበል በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ በጋራ ለመስራት መታቀዱን ገልጸዋል።
በኮሌጁ የመምህራን፣ ትምህርትና የትምህርት አመራር ልህቀት ማዕከል አስተባባሪ የሆኑት መምህር ተከተል አዳነ በበኩላቸው 'ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሆነው ሳለ ለምን በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ መሳተፍ አስፈለጋቸው?' የሚል ጥያቄ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው ት/ቤቱን ለማቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት እንደ ሀገር ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ድክመት ለማስተካከል ከታች ጀምሮ መስራት ተገቢ መሆኑ ስለታመነበት ዩኒቨርሲቲው ባለው የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ሞዴል ት/ቤት አቋቁሞ ለመስራት በመወሰኑ መሆኑን አብራርተዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አጥናፉ ዳቃሞ ት/ቤቱ ለሌሎች ትምህርት ቤቶች ሞዴል እንዲሆንና የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ኃላፊነት እንዲወጣ ታስቦ የተቋቋመ መሆኑን ገልጸው በዚህ አመት የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን በመቀበል ማስተማር የሚጀምር ሲሆን ከቀጣይ አመት ጀምሮ ደግሞ ከኬጂ(KG) አስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ ያሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተምር ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ ጨምረውም ትምህርት የጋራ ስራ የሚጠይቅ እንደመሆኑ በመምህራን፣ በተማሪዎች እና በወላጆች መካከል ሊኖር የሚገባውን ህብረትና ለአንድ አላማ የመስራት ፍላጎት ለማሳደግ መሰል ውይይቶች ሚናቸው የጎላ እንደሚሆን ገልፀዋል።
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ሰባት የሚደርሱ የወላጅ ኮሚቴ አባላት የተመረጡ ሲሆን በውይይቱ የተሳተፉ ወላጆች ዩኒቨርሲቲው ትልቅ ተነሳሽነት እና ኃላፊነት ወስዶ ሞዴል ትምህርት ቤቱን በማቋቋሙና ወላጆችን ጠርቶ ግንዛቤው እንዲኖራቸው በማድረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።