የግንዛቤ ማስጨበጫ ጉባኤ በምሩቃን ስነ መቀጠር ላይ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመቀጠር ምጣኔ ማጎልበቻና ሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ከኢንፎማይንድ ሶሊዩሽን ደረጃ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የመቀጠር ብቃት ዙሪያ የባለድርሻ አካላት ሚና ላይ የግማሽ ቀን የውይይት መድረክ በሀዋሳ ሮሪ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተካሂዷል::
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ኢ/ር ፍሰሀ ጌታቸው መድረኩን ሲከፍቱ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ግዜ በርካታ ሺህ ምሩቃንን አፍርቶ በሀገር ውስጥና በዓለም ዙርያ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የስራውን አለም እንዲቀላቀሉ ማብቃቱን አስታውሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደረገው ጥናት አዳዲስ ምሩቃን ወዲያውኑ የስራ እድል የማግኘት ምጣኔ እየቀነሰ በመምጣቱ ይህንን ችግር ለመቅረፍና ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃንን ለማፍራት በማሰብ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ማዕከል ተቋቁሞ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር ትብብር በመፍጠር አመርቂ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በኢንፎማይንድ ሶሊዩሽን የደረጃ ፕሮግራም ፓርትነርሺፕ አስተባባሪ አቶ ደምሴ አምሳሉ "ደረጃ ፕሮግራም" እ.ኤ.አ በ2017 ሲቋቋም አዳዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ከትምህርት ወደ ስራ አለም ሲቀላቀሉ የሚገጥማቸውን ተግዳሮት በማጥናት መፍትሔ ለማበጀት ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል። እስከአሁን ድረስም ድርጅታቸው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከሀያ በላይ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ከ51,000 በላይ ለሚሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች የክህሎት ስልጠናና የሙያ ማጎልበቻ ምክር በመስጠት ከ78,000 በላይ የሚሆኑ ምሩቃን ደግሞ በዚሁ ፕሮግራም አማካኝነት የስራ እድል እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል። በተሰራው ስራም የተሻሉ ውጤቶች እየተመዘገቡ በመሆኑ ይህንኑ አጠናክሮ ለመቀጠል ከመጨረሻ አመት ተማሪዎች በተጨማሪ በቀጣይ ከመጀመሪያው አመት ጀምሮ የሚገኙ ተማሪዎችን ያሳተፈ ስልጠና ለመስጠት ታቅዷል ብለዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመቀጠር ምጣኔ ማጎልበቻና የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከል ኃላፊ አቶ ክብረት ፍቃዱ በበኩላቸው ማዕከሉ ከምስረታው ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ኮሌጆች የሚገኙ የመጨረሻ አመት ተማሪዎችን በዩኒቨርሲቲው ከሚሰጠው የቀለም ትምህርት ጎንለጎን ወደ ስራው አለም ሲገቡ ሊኖራቸው በሚገቡ ክህሎቶች ላይ ከተለያዩ አጋሮች ጋር በመተባበር ተከታታይ ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ገልፀዋል። የውይይት መድረኩም ዓላማ ተማሪዎች ተወዳዳሪ ሆነው መውጣት እንዲችሉ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ታውቆ ሁሉም በበቂ ሁኔታ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ግንዛቤ መፍጠር መሆኑን አቶ ክብረት አስምረውበታል::
በጉባኤው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና የተማሪ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በምሩቃን የመቀጠር ዕድልና የስራ አለም ተወዳዳሪነት ላይ የተሰራ ጥናት ግኝት እንዲሁም በደረጃ ፕሮግራም በኩል ሥራና ሰራተኛውን ከሚፈለገው ብቃት ጋር ለማገናኘት የሚጠበቀው የስነ ልቦና ዝግጁነት እና ተፈላጊ ክህሎት ምንነት ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሃሳቦች ቀርበው በዩኒቨርሲቲው ማዕከል አስተባባሪ የነበሩ መምህራን የፓናል ውይይት ተደርጓል::
በመጨረሻም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ኮሚዩኬሽን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እመቤት በቀለ ኢንፎማይንድ ሶሊዩሽን ምን እንደሚሰራና በስራዎቹም ያስመዘገባቸው ውጤቶች ምን እንደሆኑ ግልጽ መደረጉ ሁሉንም የዩኒቨርሲቲው ባለድርሻ አባላት በሙያ ማጎልበቻ ማዕከሉ በኩል ከድርጅቱ ጋር በላቀ ትብብር ለመስራት እንደሚያነሳሳ ያላቸውን እምነት ገልጸው የበለጠ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ደግሞ የኮሚዩኬሽን ዘርፉ የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚያ ባለፈ ምሩቃን ተወዳዳሪና በሥራው አለም ተመራጭ እንዲሆኑ ለማስቻል ከቀለም ትምህርቱ እኩል የክህሎት ማጎልበቻ ሥራዎች አስፈላጊነት ላይ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው አመራርና ማህበረሰብ ጥሩ ግንዛቤ ኖሯቸው የተሻለ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉም ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልፀው ጉባኤውን ያዘጋጁ አካላትን በሙሉ በዩኒቨርሲቲው ስም አመስግነዋል::