15ኛው ዙር የገጠር መሬት አስተዳደር ሥልጠና

15ኛው ዙር የገጠር መሬት አስተዳደር ሥልጠና የመዝጊያ ፕሮግራም በወንዶገነት ደ/ተ/ሀ/ኮሌጅ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከሦስት ክልሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ለ15ኛ ዙር ሲሰጥ የነበረው የገጠር መሬት አስተዳደር ሥልጠና የመዝጊያና የ132 ሰልጣኞች ምረቃ ፕሮግራም ነሐሴ 28/2015 ዓም በኮሌጁ ሲዳ አዳራሽ ተካሂዷል::

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር ሳሙኤል በቀለ ፕሮግራሙን በከፈቱበት ንግግራቸው ኮሌጁ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እስካሁን ከወረዳና ከቀበሌ የተወጣጡ 1700 የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎችን በ15 ዙሮች ሲያሰለጥን መቆየቱን ገልጸው የዚህ ዙር ሰልጣኞችም በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ትዕግስቱ ገ/መስቀል በበኩላቸው ከመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን ችግር ለማስተካከል በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ይህንን ስራ ከውጤት ለማድረስ ዋነኛ ተዋናይ የሚሆኑ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከስድስት የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ተደጋጋሚ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ ብሔራዊ የመሬት አስተዳደር መረጃ ስርዓትን ለመዘርጋትና አንድ ወጥ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲን ለመንደፍ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በወ/ደ/ተ/ሀ/ኮሌጅ የመሬት አስተዳደርና ቅየሳ ት/ክፍል ኃላፊና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ አስራት ጆርጌ እንደገለፁት ስልጠናው ከሲዳማ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ከደቡብ ብ/ብ/ህ/ክልል ተመርጠው ለመጡ ሰልጣኞች ለአንድ ወር ያህል መሰጠቱን እና የመሬት መረጃ አያያዝን ለማዘመን ሊሰሩ ስለሚገባቸው ስራዎች በቂ እውቀትና ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን አስረድተዋል።

በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ም/ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብትና የመሬት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ውብሸት ዘነበ: የሲዳማ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ ሆዬሶ: እንዲሁም የደቡብ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኖህ ታደለ የተገኙ ሲሆን ኃላፊዎቹ ስልጠናውን ያዘጋጁና ያስተባበሩ አካላት አመስግነው መሬት የተፈጥሮ ሀብት የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ ይህንን ሀብት በአግባቡ መምራት ብሎም ህዝቡንና መንግስትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። ስልጠናውን ያገኙት ባለሙያዎችም በመሬት አስተዳደር ጉዳይ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ክልል ድረስ ለመሄድ የነበረውን እንግልት በማስቀረት በቀበሌና ወረዳ ደረጃ እንዲፈቱ ለማድረግ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወቱ እምነታቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በእለቱ ስልጠናውን ላጠናቀቁ የ15ኛው ዙር ሰልጣኞችና ለስራው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የስራ ክፍሎች የምስክር ወረቀት በመስጠት ፕሮግራሙ ተጠናቋል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et